bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Matthew 24
Matthew 24
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ፣ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ።
2
እርሱ ግን፣ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲሁ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም” አላቸው።
3
በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።
4
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤
5
ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ በማለት በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
6
ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሆኖም መጨረሻው ገና ስለሆነ በዚህ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ።
7
ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤
8
ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው።
9
“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኋል፤ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
10
በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም።
11
ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ።
12
ክፋት ስለሚገንን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤
13
እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
14
ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።
15
“እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተነገረው፣ ‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል።
16
በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚገኙ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤
17
በቤቱ ጣራ ላይ የሚገኝ ማንም ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ፤
18
በዕርሻ ቦታው የሚገኝ ማንም ሰው ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ።
19
በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!
20
እንግዲህ ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ፤
21
በዚያን ጊዜ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል።
22
ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበረ፤ ስለተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።
23
በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤
24
ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ።
25
እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።
26
“ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ በረሓው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤
27
መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል።
28
በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ።
29
“ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኅይላትም ይናጋሉ።’
30
“በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤
31
መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱም ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ።
32
“ከበለስ ዛፍ ይህን ትምህርት ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ።
33
እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ።
34
እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።
35
ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።
36
“ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም።
37
ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤
38
ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣
39
እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል።
40
በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።
41
ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች።
42
“እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ።
43
ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር።
44
የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።
45
“በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ እንግዲህ ማነው?
46
ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው፤
47
እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።
48
ነገር ግን ያ አገልጋይ ክፉ ቢሆንና ለራሱ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣
49
ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣
50
እርሱ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣
51
ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
← Chapter 23
Chapter 25 →