bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Matthew 17
Matthew 17
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ረዥም ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ።
2
በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።
3
ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።
4
ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ በዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው።
5
እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።
6
ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።
7
ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው።
8
ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም።
9
ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው።
10
ደቀ መዛሙርቱም፣ “ታዲያ የኦሪት ሕግ መምህራን፣ ኤልያስ አስቀድሞ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
11
እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ መጥቶ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፤
12
ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቷል፤ ሆኖም የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። እንዲሁም የሰው ልጅ በእጃቸው መከራን ይቀበላል።”
13
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ተረዱ።
14
ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤
15
“ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤
16
ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።”
17
ኢየሱስም፣ “አንት የማታምን ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤ እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ። ልጁን ወደዚህ አምጡት” አለ።
18
ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸውና ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነ።
19
ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
20
እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤
21
የዚህ ዐይነቱ ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በስተቀር አይወጣም።”
22
በገሊላ ተሰባስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “የሰውን ልጅ አሳልፈው ለሰዎች ይሰጡታል፤
23
ይገድሉታልም፤ እርሱም በሦስተኛው ቀን ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱም እጅግ ዐዘኑ።
24
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱ ግብር ተቀባዮች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” አሉት።
25
እርሱም፣ “ይከፍላል እንጂ” አላቸው። ጴጥሮስ ወደ ቤት እንደ ገባ ኢየሱስ በቅድሚያ፣ “ስምዖን፤ የምድር ነገሥታት ግብር ወይም ቀረጥ የሚቀበሉት ከራሳቸው ልጆች ወይስ ከሌሎች ይመስልሃል?” አለው።
26
ጴጥሮስም፣ “ከሌሎች ነው የሚቀበሉት” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እንግዲያውስ ልጆች ነጻ ናቸው፤
27
ሆኖም እንዳናስቀይማቸው ሄደህ መንጠቈህን ወደ ባሕር ጣል፤ መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት የምታገኘውን አንድ እስታቴር በእኔና በአንተ ስም ክፈል።”
← Chapter 16
Chapter 18 →