bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Matthew 12
Matthew 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ ዐለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር።
2
ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን መደረግ የሌለበትን እያደረጉ ነው” አሉት።
3
እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ፣ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን?
4
ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባ፤ ለካህናት እንጂ ለእርሱም ሆነ አብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት በላ።
5
ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም?
6
ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ።
7
‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሓን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር።
8
የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”
9
ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤
10
በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከስሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዷል?” ብለው ጠየቁት።
11
እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት፣ በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጐትቶ አያወጣውምን?
12
ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዷል” አላቸው።
13
ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላኛውም እጁ ደኅና ሆነለት።
14
ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።
15
ኢየሱስ ሐሳባቸውን ዐውቆ ከዚያ ዘወር አለ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤
16
ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።
17
ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤
18
“እነሆ፤ የመረጥሁት፣ የምወድደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል።
19
አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም።
20
ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም።
21
አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”
22
ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ።
23
ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።
24
ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ።
25
ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በእርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም።
26
ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በእርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል?
27
እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በምን ሊያስወጧቸው ነው? ስለዚህ ልጆቻችሁ ይፈርዱባችኋል።
28
እኔ ግን አጋንንትን የማስወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች።
29
“ወይስ አንድ ሰው ወደ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ለመዝረፍ ቢፈልግ፣ አስቀድሞ ያንን ኀይለኛ ሰው ሳያስር እንዴት አድርጎ ይሳካለታል? ኋላም ቤቱን መበዝበዝ ይችላል።
30
“ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ሁሉ ይበትናል።
31
ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም።
32
ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም።
33
“ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ።
34
እናንት የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና።
35
መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር በጎ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር መጥፎ ነገር ያወጣል።
36
ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል።
37
ምክንያቱም ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃልና።”
38
ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት።
39
እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።
40
ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል።
41
የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።
42
በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።
43
“ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ፣ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም።
44
ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል።
45
ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”
46
ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።
47
አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።
48
ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት።
49
በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤
50
በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”
← Chapter 11
Chapter 13 →