bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Mark 12
Mark 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚያም እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ ዙሪያውን ዐጠረ፤ ለመጭመቂያው ጕድጓድ ቈፈረ፤ የመጠበቂያም ማማ ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
2
በመከር ጊዜም ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ ገበሬዎቹ ላከ።
3
እነርሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት።
4
እንደ ገናም ሌላ አገልጋይ ላከ። እነርሱም ራሱን ፈንክተውና አዋርደው መለሱት።
5
አሁንም እንደ ገና ሌላ ላከ፤ ይህኛውንም ገደሉት፤ ከሌሎች ከብዙዎቹ መካከል አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹንም ገደሉ።
6
“አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወድደው ልጁ ነበረ፤ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው።
7
“ገበሬዎቹ ግን እርስ በርሳቸው፣ ‘ይህማ ዋናው ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው፤ ርስቱ የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ፤
8
ከዚያም ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ስፍራም አውጥተው ጣሉት።
9
“እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።
10
እንዲህ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን፤ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ፤
11
ጌታ ይህን አድርጓል፣ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው’?”
12
ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ስላወቁ፣ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ትተውት ሄዱ።
13
ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ።
14
እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ የሰዎች ማንነት ስለማይገድህም አታዳላም፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?
15
እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፣ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው።
16
እነርሱም አመጡለት፣ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት።
17
ኢየሱስም፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ።
18
ከዚህ በኋላ የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤
19
“መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ይህ ሰው ሴትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል።
20
ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤
21
ሁለተኛውም ሴትየዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤
22
ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች።
23
እንግዲህ፣ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሣኤ ለማናቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት።
24
ኢየሱስም፣ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ ነው!
25
ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም።
26
ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን?
27
እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል።”
28
ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዞች ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።
29
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤
30
አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’
31
ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።”
32
ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤
33
እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”
34
ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።
35
ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ?
36
ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ’ አለው። ይላል፤
37
ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።
38
በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወድዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤
39
በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፣ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤
40
በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”
41
ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ፣ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሣጥን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤
42
አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ቤሳዎች አስገባች።
43
ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ሣጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች።
44
እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድኽነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”
← Chapter 11
Chapter 13 →