bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Luke 8
Luke 8
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ ዐለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤
2
እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣
3
የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ።
4
ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤
5
“አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት።
6
አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ።
7
ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው።
8
ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።” ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
9
ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት።
10
እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’
11
“እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው።
12
በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው።
13
በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው።
14
በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም።
15
በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
16
“መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።
17
የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና።
18
እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
19
ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም።
20
በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው።
21
እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።
22
ከዕለታቱ በአንድ ቀን፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ላይ ወጣ፤ ኢየሱስም፤ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ከዚያም ጕዞ ቀጠሉ።
23
እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወስዶት ተኛ፤ በዚህ ጊዜ በባሕሩ ላይ ማዕበል ተነሣ፤ ውሃውም ጀልባዋን ዘልቆ ስለ ገባ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ደረሱ።
24
ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፣ “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ ማለቃችን እኮ ነው!” እያሉ ቀሰቀሱት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውሃውን መናወጥ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱም ነውጡም ተወ፤ ጸጥታም ሆነ።
25
እርሱም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነርሱም በፍርሀትና በመደነቅ፣ “ይህ ነፋስንና ውሃን የሚያዝ፣ እነርሱም የሚታዘዙለት እርሱ ማን ነው?” ተባባሉ።
26
ከዚህ በኋላ ከገሊላ ባሻገር ወዳለው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በጀልባ ተሻገሩ።
27
ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ፣ አጋንንት ያደረበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ አገኘው፤ ይህ ሰው ለብዙ ጊዜ ልብስ ሳይለብስ፣ በቤትም ሳይኖር የመቃብርን ስፍራ ቤቱ ያደረገ ነበር።
28
ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ ፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ጋር ምን ጕዳይ አለህ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ።
29
ርኩሱ መንፈስ ይህን ያለው ከሰውየው እንዲወጣ ኢየሱስ አዝዞት ስለ ነበር ነው። ርኩሱ መንፈስ በየጊዜው ስለሚነሣበት ሰውየው በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ቢጠበቅም፣ የታሰረበትን ሰንሰለት እየበጣጠሰ ያደረበት ጋኔን ወደ በረሓ ይነዳው ነበር።
30
ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው።
31
አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዝዛቸው አጥብቀው ለመኑት።
32
በዚያም አካባቢ በተራራ ወገብ ላይ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሣማው መንጋ ግቡ ብሎ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው።
33
አጋንንቱም ከሰውየው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ የዐሣማውም መንጋ በገደሉ አፋፍ ቍልቍል በመንደርደር ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ።
34
እረኞቹም የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ፣ ሸሽተው በመሄድ በከተማውና በገጠሩ አወሩ።
35
ሕዝቡም የተደረገውን ነገር ለማየት ከያሉበት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶ፣ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በኢየሱስም እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ።
36
በአጋንንት የተያዘው ሰው ሲድን ያዩትም፣ እንዴት እንደ ዳነ ለሕዝቡ አወሩላቸው።
37
የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎችም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ስላደረባቸው፣ ከዚያ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ወደ ጀልባው ገብቶ ተመልሶ ሄደ።
38
አጋንንት የወጡለትም ሰው አብሮት ለመሆን ኢየሱስን ለመነው፤ እርሱ ግን እንዲህ ሲል አሰናበተው፤
39
“ወደ ቤትህ ተመልሰህ፣ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላቅ ነገር ተናገር።” ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ታላቅ ነገር በከተማው ሁሉ በይፋ እየተናገረ ሄደ።
40
ሕዝቡ ሁሉ መምጣቱን ይጠባበቁ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ በደስታ ተቀበሉት።
41
በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵራብ አለቃ መጥቶ፣ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ለመነው፤
42
ይህን ልመና ያቀረበው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ አንዲት ልጅ ስለ ነበረችው ነው፤ እርሷ በሞት አፋፍ ላይ ነበረች። ወደዚያው እያመራ ሳለ፣ ሕዝቡ በመጋፋት እጅግ ያጨናንቀው ነበር።
43
ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ ሊፈውሳትም የቻለ ማንም አልነበረም።
44
እርሷም ከበስተ ኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ይፈስስ የነበረው ደሟም ወዲያው ቆመ።
45
ኢየሱስም፣ “የነካኝ ማነው?” አለ። ሁሉም መንካታቸውን በካዱ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከብቦህ በግፊያ እያስጨነቀህ ነው” አለው።
46
ኢየሱስ ግን፣ “አንድ ሰው ነክቶኛል፤ ኀይል ከእኔ እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አለ።
47
ሴትዮዋም ሳትታወቅ መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ፣ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች።
48
እርሱም፣ “ልጄ ሆይ እምነትሽ ፈውሶሻል በሰላም ሂጂ” አላት።
49
ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ፣ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታድክመው” አለው።
50
ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፣ “አትፍራ፣ እመን ብቻ እንጂ፤ ልጅህ ትድናለች” አለው።
51
ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲገባም ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቱ አባትና እናት በቀር ማንም አብሮት እንዲገባ አልፈቀደም።
52
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፣ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።
53
ሰዎቹም መሞቷን ስላወቁ ሣቁበት።
54
እርሱ ግን እጇን ይዞ፣ “ልጄ ሆይ፤ ተነሺ” አላት።
55
የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሥታ ቆመች፤ ኢየሱስም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት አዘዛቸው።
56
ወላጆቿም ተደነቁ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳያወሩ አዘዛቸው።
← Chapter 7
Chapter 9 →