bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Luke 11
Luke 11
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም እንደ ጨረሰ፣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም መጸለይን አስተምረን” አለው።
2
እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤ “ ‘አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤
3
የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን፤
4
በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና። ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።’ ”
5
ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ቢኖረውና በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤
6
አንድ ባልንጀራዬ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝምና’ ብሎ ለመነው እንበል።
7
“በቤት ውስጥ ያለውም፣ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተቈልፏል፤ ልጆቼም አብረውኝ ተኝተዋል፤ ከእንግዲህ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋልን?
8
እላችኋለሁ፤ ወዳጁ በመሆኑ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።
9
“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤
10
ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
11
“ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን?
12
ወይስ ዕንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?
13
እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”
14
አንድ ቀን ኢየሱስ ድዳ ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣለት በኋላ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም ተገረመ።
15
አንዳንዶቹ ግን፣ “በአጋንንት አለቃ፣ በብዔልዜቡል ፣ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፤
16
አንዳንዶቹ ደግሞ ሊፈታተኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ከእርሱ ይፈልጉ ነበር።
17
ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ የሚለያይ ቤትም ይወድቃል።
18
ሰይጣንም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ፣ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ ትናገራላችሁና።
19
እንግዲህ እኔ አጋንንትን የማወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በማን ያወጧቸው ይሆን? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።
20
እኔ ግን አጋንንትን የማወጣው በእግዚአብሔር ጣት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ መጣች ዕወቁ።
21
“ብርቱ ሰው በሚገባ ታጥቆ ቤቱን ከጠበቀ፣ ንብረቱ በሰላም ይቀመጣል።
22
ነገር ግን ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው መጥቶ ካጠቃውና ካሸነፈው ታምኖበት የነበረውን ትጥቁን ያስፈታዋል፤ ምርኮውንም ወስዶ ለሌሎች ያካፍላል።
23
“ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ይበትናል።
24
“ርኩስ መንፈስ ከሰው ሲወጣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሳያገኝም ሲቀር፣ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤
25
ሲመለስም ቤቱ ተጠራርጐና ተስተካክሎ ያገኘዋል።
26
ከዚያም በኋላ ሄዶ ሌሎች ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያ ሰው ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆንበታል።”
27
ኢየሱስ ይህን እየተናገረ እያለ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” አለችው።
28
እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ።
29
ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ በሄደ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ታምራዊ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ አይሰጠውም።
30
ምክንያቱም ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል።
31
የደቡቧ ንግሥት በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ እርሷ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።
32
የነነዌ ሰዎችም በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።
33
“መብራት አብርቶ በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁን የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።
34
የሰውነትህ ብርሃን ዐይንህ ናት፤ ዐይንህ ጤናማ ስትሆን መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፤ ዐይንህ ታማሚ ከሆነች ግን መላ ሰውነትህ የጨለመ ይሆናል።
35
ስለዚህ በውስጥህ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ።
36
እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ከሆነና የጨለመ የሰውነት ክፍል ከሌለበት፣ የሰውነትህ ሁለንተና መብራት በወገግታው ያበራልህ ያህል ይደምቃል።”
37
ኢየሱስ ንግግሩን እንደ ጨረሰ፣ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምግብ እንዲበላ ጋበዘው፤ እርሱም አብሮት ገብቶ በማእድ ተቀመጠ።
38
ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ።
39
ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በሥሥትና በክፋት የተሞላ ነው።
40
እናንት ሞኞች፤ የውጭውን የፈጠረ የውስጡንም አልፈጠረምን?
41
ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል።
42
“እናንት ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ፤ ከአዝሙድና ከጤና አዳም እንዲሁም ከአትክልት ሁሉ ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ ሆኖም ፍትሕንና እግዚአብሔርን መውደድ ቸል ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያንን ሳትተዉ ይህኛውን ማድረግ በተገባችሁ ነበር።
43
“እናንት ፈሪሳውያን ወዮላችሁ፤ በምኵራብ የክብር መቀመጫ፣ በገበያ መካከልም እጅ መነሣትን ትወድዳላችሁና።
44
“ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበትን የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ።”
45
ከሕግ ዐዋቂዎች አንዱ መልሶ “መምህር ሆይ፤ እንዲህ ስትናገር እኮ እኛንም መስደብህ ነው” ሲል መለሰለት።
46
ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እናንት ሕግ ዐዋቂዎችም ደግሞ ወዮላችሁ፤ ሰዎች ሊሸከሙ የማይችሉትን ከባድ ሸክም ታሸክማላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ ግን በጣታችሁ እንኳ አትነኩትም።
47
“አባቶቻችሁ የገደሏቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምታበጃጁ፣ ወዮላችሁ፤
48
እንግዲህ የአባቶቻችሁን ሥራ የምታጸኑ ምስክሮች ናችሁ፤ እነርሱ ነቢያትን ገደሉ፤ እናንተም መቃብራቸውን ታበጃጃላችሁ።
49
ስለዚህም የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፤ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን እልክላቸዋለሁ፤ እነርሱ አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ሌሎችንም ያሳድዳሉ።’
50
ስለዚህ ይህ ትውልድ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስለ ፈሰሰው፣ ስለ ነቢያት ሁሉ ደም ተጠያቂ ነው፤
51
ከአቤል ደም ጀምሮ፣ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ፈሰሰው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ይፈለግበታል፤ አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ለዚህ ተጠያቂ ነው።
52
“እናንት ሕግ ዐዋቂዎች ወዮላችሁ፤ የዕውቀትን መክፈቻ ነጥቃችሁ ወስዳችኋልና፤ እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁበትም፤ የሚገቡትንም ከልክላችኋል።”
53
ኢየሱስ ከዚያ ከወጣ በኋላ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ክፉኛ ይቃወሙትና በጥያቄም ያዋክቡት ጀመር፤
54
ከአፉ በሚወጣውም ቃል ሊያጠምዱት ያደቡ ነበር።
← Chapter 10
Chapter 12 →