bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Leviticus 25
Leviticus 25
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፤
2
“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራሷ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሰንበት ታክብር።
3
ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ።
4
በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ።
5
ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ።
6
ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋር ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤
7
እንዲሁም ለቤት እንስሶችህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን።
8
“ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቍጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ።
9
ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን፣ መለከት ይነፋ፤ በማስተስረያ ቀንም በምድራችሁ ሁሉ መለከት ንፉ።
10
አምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ።
11
የአምሳኛው ዓመት ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ አትዝሩ፤ ሳትዘሩት የበቀለውን አትጨዱ፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬ አትሰብስቡ።
12
ኢዮቤልዩ ስለሆነ ለእናንተ የተቀደሰ ይሁን፤ ሳትዘሩት በሜዳ የበቀለውን ብሉ።
13
“ ‘በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ።
14
“ ‘ከወገንህ ከአንዱ መሬት ብትገዛ ወይም ብትሸጥለት፣ አንዱ ሌላውን አያታልል።
15
ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ከወገንህ ትገዛለህ፤ እርሱም የቀሩትን የመከር ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ይሸጥልሃል።
16
የዓመቱ ቍጥር ከበዛ ዋጋውን ጨምር፤ የዓመቱ ቍጥር ካነሰም፣ ዋጋውን ቀንስ፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ የዓመቱን የምርት መጠን ነውና።
17
አንዱ ሌላውን አያታልል፤ አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
18
“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራላችሁ።
19
ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም በሰላም ትኖራላችሁ።
20
እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል።
21
በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች።
22
በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ።
23
“ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ።
24
ርስት አድርጋችሁ በምትይዙት ምድር ሁሉ መሬት የሚዋጅበት ሁኔታ እንዲኖር አድርጉ።
25
“ ‘ከወገንህ አንዱ ደኽይቶ ርስቱን ቢሸጥ፣ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወገኑ የሸጠውን ይዋጅለት።
26
ነገር ግን ሰውየው ርስቱን የሚዋጅለት ምንም ዘመድ ባይኖረውና እርሱ ራሱ መዋጀት የሚችልበትን ሀብት ቢያገኝ፣
27
ርስቱን ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሽያጭ ዘመን በመቍጠር የዋጋውን ልዩነት ለገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ገዛ ርስቱ ይመለስ።
28
ነገር ግን ዋጋውን መመለስ ካልቻለ፣ የሸጠው ርስት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የገዥው ንብረት ሆኖ ይቈያል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ለባለቤቱ ይመለሳል፤ ሰውየውም ወደ ርስቱ ይመለሳል።
29
“ ‘ማንኛውም ሰው ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤቱን ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ሊዋጀው ይችላል፤ የመዋጀት መብቱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ነው።
30
አንዱ ዓመት ከማለቁ በፊት መዋጀት ካልቻለ ግን፣ ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ ያለው ቤት የገዢውና የልጅ ልጆቹ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ አይመለስለትም።
31
ቅጥር በዙሪያው ባልተሠራለት መንደር ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን እንደ ዕርሻ መሬት ተቈጥረው ሊዋጁ ይችላሉ፤ በኢዮቤልዩም ይመለሳሉ።
32
“ ‘ነገር ግን ሌዋውያን የራሳቸው በሆኑት ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ቤቶቻቸውን ምንጊዜም የመዋጀት መብት አላቸው።
33
ሌዋውያን በከተማቸው ያለውን ቤታቸውን ቢሸጡና መዋጀት ባይችሉ፣ በኢዮቤልዩ ይመለሳል፤ በሌዋውያን ከተሞች የሚገኙ ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የሌዋውያን ንብረት ናቸውና።
34
በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት ግን አይሸጥ፤ ለዘላለም ቋሚ ንብረታቸው ነውና።
35
“ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደምትረዳ እርዳው።
36
ወገንህ በመካከልህ ይኖር ዘንድ ምንም ዐይነት ወለድ አትቀበለው፤ አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራው።
37
ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት።
38
የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ (ኤሎሂም) ልሆን፣ ከግብፅ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
39
“ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው።
40
በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቍጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤
41
ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ።
42
እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለ ሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ።
43
በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ።
44
“ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ።
45
እንደዚሁም በመካከላችሁ ከሚኖሩት መጻተኞችና ከተወለዱት ወገናቸው ባሪያዎችን ግዙ፤ ንብረታችሁም ይሁኑ።
46
እነርሱንም እንደ ንብረት ለልጆቻችሁ አውርሷቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ባሪያዎች ይሁኗችሁ፤ እስራኤላውያን ወገኖቻችሁን ግን በጭካኔ አትግዟቸው።
47
“ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆንና ከወገናችሁ አንዱ ደኽይቶ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ወይም ከመጻተኛው ወገን ለአንዱ ራሱን ቢሸጥ፣
48
ከተሸጠ በኋላ ሊዋጅ ይችላል። ከዘመዶቹም አንዱ፣
49
አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ወይም ከወገኖቹ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ ይዋጀው፤ ሀብት ካገኘም ራሱን መዋጀት ይችላል።
50
እርሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንሥቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር በመሆን ይቍጠር፤ ነጻ የሚለቀቅበትም ዋጋ በእነዚያ ዓመታት ለአንድ ቅጥር ሠራተኛ በሚከፈለው መሠረት ይተመናል።
51
ብዙ ዓመት የሚቀረው ከሆነም፣ እርሱን ለመግዛት ከተከፈለው ዋጋ ላይ በቀረው ዓመት መጠን ለሚዋጅበት መልስ ይክፈል።
52
እስከ ኢዮቤልዩ ድረስ የሚቀረው ጥቂት ዓመት ከሆነም፣ በቀረው ዓመት መጠን የሚዋጅበትን መልስ ይክፈል።
53
ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ይኑር፤ አሳዳሪውም በፊትህ በጭካኔ አይግዛው።
54
“ ‘ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ እንኳ መዋጀት ባይችል፣ እርሱና ልጆቹ በኢዮቤልዩ ዓመት በነጻ ይለቀቁ፤
55
እስራኤላውያን ለእኔ አገልጋዮቼ ናቸውና። እነርሱ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
← Chapter 24
Chapter 26 →