bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Leviticus 10
Leviticus 10
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ።
2
ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ሞቱ።
3
ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፦ “ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣ እከበራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ።
4
ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው።
5
እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።
6
ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ ጠጕራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ።
7
የእግዚአብሔር (ያህዌ) የመቅቢያ ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን አትውጡ።” እነርሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።
8
እግዚአብሔርም (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤
9
“እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።
10
የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኩሱንና ንጹሑን ለዩ፤
11
እግዚአብሔርም (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።”
12
ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የእህል ቍርባን የቀረውን ወስዳችሁ ያለ እርሾ ጋግሩት፤ እጅግ ቅዱስ ስለሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት።
13
ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት ያንተና የልጆችህ ድርሻ ይህ ስለሆነ፣ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት፤ እንዲህ ታዝዣለሁና።
14
ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የእናንተ ድርሻ ሆኖ ስለ ተሰጠ፣ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ብሉት።
15
የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋር ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”
16
ሙሴ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበውን ፍየል አጥብቆ ፈለገ፤ መቃጠሉንም በተረዳ ጊዜ የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤
17
“የኀጢአት መሥዋዕቱን ለምን በተቀደሰው ስፍራ አልበላችሁትም? እጅግ የተቀደሰ ነው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ስርየት በማስገኘት የሕዝቡን ኀጢአት እንድታስወግዱበት የተሰጣችሁ ነበር፤
18
ደሙ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ስላልገባ፣ በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት ፍየሉን በተቀደሰው ስፍራ መብላት ይገባችሁ ነበር።”
19
አሮንም ሙሴን፣ “እነሆ፤ በዛሬው ቀን የኀጢአት መሥዋዕታቸውንና የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ፤ እኔም እንዲህ ያለ ነገር የደረሰብኝ ሰው ነኝ፤ ታዲያ፣ ዛሬ የኀጢአት መሥዋዕቱን ብበላ ኖሮ እግዚአብሔርስ (ያህዌ) ደስ ይለው ኖሯልን?” አለው።
20
ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው።
← Chapter 9
Chapter 11 →