bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Judges 7
Judges 7
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ይሩበኣል የተባለው ጌዴዎን፣ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጧት ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያንም ሰፈር እስራኤላውያን ከሰፈሩበት በስተ ሰሜን በኩል፣ በሞሬ ኰረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበር።
2
እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳልሰጥ አብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ እስራኤላውያን የገዛ ኀይላቸው እንዳዳናቸው በመቍጠር እንዳይታበዩብኝ፣
3
‘ማንም የፈራ ቢኖር የገለዓድን ተራራ ትቶ ወደ መጣበት ይመለስ’ ብለህ ለሕዝቡ ዐውጅ።” ስለዚህ ሃያ ሁለቱ ሺሕ ሲመለሱ ዐሥሩ ሺሕ ብቻ ቀሩ።
4
እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “አሁንም ሰዎቹ ብዙ ናቸው፤ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ውረድ፤ በዚያም እለይልሃለሁ። ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ነገር ግን፣ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋር አይሄድም።”
5
ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ ይዟቸው ወረደ፤ እዚያም እግዚአብሔር ፤ “ውሻ በምላሱ እየጨለፈ እንደሚጠጣ ሁሉ፣ በምላሳቸው የሚጠጡትን፣ በጕልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው።
6
ሦስት መቶ ሰዎች ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ ጠጡ፤ የቀሩት ሁሉ ግን ለመጠጣት በጕልበታቸው ተንበረከኩ።
7
እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፣ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደየመጡበት ይመለሱ” አለው።
8
ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ። በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቋማው ውስጥ ነበር።
9
በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ፤ በሰፈሩም ላይ ውረድ፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና።
10
አደጋ ለመጣል የምትፈራ ከሆነ ግን፣ ፉራ ከተባለው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤
11
የሚሉትንም አድምጥ፤ ከዚያ በኋላ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ።” ስለዚህም ጌዴዎን አገልጋዩን ፉራን አስከትሎ እስከ ሰፈሩ ዳርቻ ወረደ።
12
ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም።
13
አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፣ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፣ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታቱም ኀይለኛነት የተነሣ ድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር።
14
ጓደኛውም መልሶ፣ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው።
15
ጌዴዎንም ሕልሙንና ፍቺውን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ወጥቶ፣ “ እግዚአብሔር የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷልና ተነሡ” አላቸው።
16
ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፍሎ፣ እያንዳንዱን ሰው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ ያለበት ባዶ ማሰሮ በእጁ እንዲይዝ አደረገ።
17
ጌዴዎንም እንዲህ አላቸው፤ “እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ እኔ የማደርገውን አይታችሁ ልክ እንደዚያው አድርጉ።
18
እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን በምንነፋበት ጊዜ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችሁን እየነፋችሁ፣ ‘ ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን’ ብላችሁ ጩኹ።”
19
ዘቦቹ ተቀያይረው የእኩለ ሌሊቱን ጥበቃ በጀመሩበት ጊዜ፣ ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት መቶ ሰዎች በሰፈሩ ዳርቻ ደረሱ፤ እነርሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ማሰሮች ሰበሩ።
20
በሦስት ቡድን የተከፈሉት ሰዎች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ማሰሮቻቸውንም ሰበሩ፤ ችቦዎቻቸውን በግራ እጆቻቸው፣ የሚነፏቸውንም ቀንደ መለከቶች በቀኝ እጆቻቸው ይዘው፣ “ የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጮኹ።
21
እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ የተመደበበትን ቦታ እንደ ያዘም ምድያማውያኑ እየጮኹ ሸሹ።
22
የሦስት መቶው ቀንደ መለከት ድምፅ እንደ ተሰማም እግዚአብሔር በሰፈሩ ውስጥ ያለው ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሰራዊቱ በጽሬራ አቅጣጫ ወደ ቤት ሺጣ፣ ከዚያም ዐልፈው በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤላሞሖላ ድንበር ድረስ ሸሽተው ሄዱ።
23
በንፍታሌም፣ በአሴርና በመላው የምናሴ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ተጠርተው ወጡ፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ።
24
ጌዴዎንም በኤፍሬም ኰረብታማ አገር ለሚኖሩት ሁሉ፣ “በምድያማውያን ላይ ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስ ወንዝ ቀድማችሁ ያዙ” አላቸው። ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጡ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስን ወንዝ ያዙ።
25
እንዲሁም ሔሬብና ዜብ የተባሉትን ሁለቱን የምድያም መሪዎች ያዙ። ሔሬብን በሔሬብ ዐለት አጠገብ፣ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሏቸው፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብን ራስ ቈርጠው ጌዴዎን ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ይዘው መጡ።
← Chapter 6
Chapter 8 →