bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Judges 15
Judges 15
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ለማየት ሄደ፤ እርሱም፣ “ሚስቴ ወዳለችበት ጫጕላው ቤት ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም።
2
አባትየውም፣ “ፈጽሞ የጠላሃት መሆንህን ስለ ተረዳሁ ለሚዜህ ድሬለታለሁ፤ ታናሽ እኅቷ ከእርሷ ይልቅ ውብ አይደለችምን? እርሷን አግባት” አለው።
3
ሳምሶንም መልሶ፣ “ከእንግዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ በሚደርሰው ጕዳት ተጠያቂ አልሆንም” አላቸው።
4
ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋር አሰረው።
5
ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ።
6
ፍልስጥኤማውያን፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፣ “ሚስቱ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የተምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ። ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው።
7
ሳምሶንም፣ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ።
8
ክፉኛ መታቸው፤ ከነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኢታም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ።
9
ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ።
10
የይሁዳም ሰዎች፣ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ልናስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው።
11
ከዚያም ሦስት ሺሕ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤታም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፣ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ሳምሶንም፣ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው።
12
እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት። ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።
13
እነርሱም፣ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት።
14
ሳምሶን ሌሒ እንደ ደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ።
15
ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺሕ ሰው ገደለ።
16
ሳምሶንም፣ “በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ ሺሕ ሰው ዘራሪ፤ በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ ሺሕ ሬሳ አነባባሪ ” ብሎ ፎከረ።
17
ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒ ተብሎ ተጠራ።
18
እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
19
እግዚአብሔርም በሌሒ ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውሃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ። ስለዚህ ያ ምንጭ ዓይንሀቆሬ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው በሌሒ ይገኛል።
20
ሳምሶንም በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ።
← Chapter 14
Chapter 16 →