bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Joshua 5
Joshua 5
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
በዚህ ጊዜ ከዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ያሉት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፣ በባሕሩም ዳርቻ ያሉ የከነዓናውያን ነገሥታት በሙሉ እግዚአብሔር ዮርዳኖስን እስክንሻገር ወንዙን በእስራኤላውያን ፊት እንዴት እንዳደረቀው በሰሙ ጊዜ፣ ልባቸው በፍርሀት ቀለጠ፤ እስራኤላውያንንም ለመቋቋም ድፍረት ዐጡ።
2
በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “የባልጩት መቍረጫ አዘጋጅተህ፣ ያልተገረዙትን እስራኤላውያንን ለሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው” አለው።
3
ስለዚህ ኢያሱ የባልጩት መቍረጫ አዘጋጅቶ በጊብዓዝ ዓረሎት በተባለ ስፍራ እስራኤላውያንን ገረዛቸው።
4
እንግዲህ ኢያሱ እስራኤላውያንን የገረዘበት ምክንያት ይህ ነው፤ ዕድሜያቸው መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ ሞቱ።
5
ከዚያ የወጡት ሰዎች ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ በጕዞ ላይ ሳሉ የተወለዱት ግን በሙሉ አልተገረዙም ነበር።
6
ግብፅን ለቀው በወጡ ጊዜ መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፣ እነርሱ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይንከራተቱ ነበር። እግዚአብሔር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው ቃል የገባላቸውን ያችን ማርና ወተት የምታፈስስ ምድር እንደማያዩአት ምሏልና።
7
ስለዚህ በእነርሱ ምትክ ወንዶች ልጆቻቸውን አስነሣ። እንግዲህ ኢያሱ የገረዛቸው እነዚህን ነበር፤ በጕዞ ላይ ሳሉ ባለመገረዛቸው ከነሸለፈታቸው ነበሩና።
8
ሕዝቡ ሁሉ ከተገረዙ በኋላ ቍስሉ እስኪሽር ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቈዩ።
9
ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነሆ፤ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” አለው፤ ከዚህም የተነሣ የዚያ ቦታ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተባለ።
10
እስራኤላውያን በኢያሪኮ ሜዳ በጌልገላ ሰፍረው ሳሉ፣ ወሩ በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የፋሲካን በዓል አከበሩ።
11
ከፋሲካም በኋላ በዚያኑ ዕለት የምድሪቱን ፍሬ ማለት ያልቦካ ቂጣና የተጠበሰ እሸት በሉ።
12
የምድሪቱን ፍሬ በበሉበት ቀን መናው መውረዱ ቀረ፤ ከዚያ በኋላ ለእስራኤላውያን መና አልወረደላቸውም፤ ነገር ግን በዚያኑ ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።
13
ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ፣ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ከፊቱ ቆሞ አየ። ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው።
14
እርሱም፣ “አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃ በመሆኔ እነሆ፤ መጥቻለሁ” ሲል መለሰለት፤ ኢያሱም በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደና፣ “ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድን ነው?” አለው።
15
የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃም ኢያሱን፣ “ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤ የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ናትና” አለው፤ ኢያሱም እንደ ታዘዘው አደረገ።
← Chapter 4
Chapter 6 →