bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
John 11
John 11
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
በማርያምና በእኅቷ በማርታ መንደር በቢታንያ ይኖር የነበረው አልዓዛር ታሞ ነበር።
2
ይህች ወንድሟ አልዓዛር የታመመባት ማርያም፣ በጌታ ላይ ሽቱ አፍስሳ እግሩን በጠጕሯ ያበሰችው ነበረች።
3
እኅትማማቾቹም፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትወድደው ሰው ታምሟል” ብለው መልእክት ላኩበት።
4
ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ “ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት የሚያደርስ አይደለም” አለ።
5
ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወድዳቸው ነበር።
6
ሆኖም አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ፣ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ቈየ።
7
ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው።
8
እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩህ እየፈለጉህ ነበር፤ እንደ ገና ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት።
9
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ብርሃን አይደለምን? ከዚህ ዓለም ብርሃን የተነሣ ስለሚያይ በቀን የሚመላለስ አይሰናከልም፤
10
የሚሰናከለው ግን በሌሊት የሚመላለስ ነው፤ ብርሃን የለውምና።”
11
ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው።
12
ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል” አሉት።
13
ኢየሱስ ይህን የነገራቸው ስለ ሞቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ መሰላቸው።
14
ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ “አልዓዛር ሞቷል፤
15
ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ባለ መኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።”
16
ከዚያም ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ሄደን ከእርሱ ጋር እንሙት” አላቸው።
17
ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር።
18
ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ትርቅ ነበር።
19
ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤
20
ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር።
21
ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር።
22
አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።”
23
ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት።
24
ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው።
25
ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤
26
በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?”
27
እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው።
28
ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት።
29
ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች።
30
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር።
31
ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት።
32
ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው።
33
ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በሐዘን ታውኮ፣
34
“የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት።
35
ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።
36
አይሁድም፣ “እንዴት ይወድደው እንደ ነበር አያችሁ” አሉ።
37
ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዐይነ ስውሩን ዐይን የከፈተ፣ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ።
38
ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤
39
እርሱም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹም እኅት ማርታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” አለችው።
40
ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” አላት።
41
ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤
42
ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።”
43
ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ።
44
የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው።
45
ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፣ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩት አይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።
46
አንዳንዶቹ ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ለፈሪሳውያን ተናገሩ፤
47
ከዚያም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል?
48
እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ስፍራችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።”
49
ከመካከላቸውም አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እናንተ እኮ ምንም አታውቁም!
50
ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።”
51
ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤
52
ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው።
53
ከዚያን ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ።
54
ስለዚህ ኢየሱስ ከዚያ ወዲያ በአይሁድ መካከል በይፋ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን በምድረ በዳ አጠገብ ወደምትገኝ ኤፍሬም ወደ ተባለች መንደር ገለል አለ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሰነበተ።
55
የአይሁድ ፋሲካ እንደ ተቃረበም፣ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የመንጻት ሥርዐት ለማድረግ ብዙዎች ከአገር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።
56
ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው፣ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓሉ አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ።
57
የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን ይይዙት ዘንድ የት እንዳለ የሚያውቅ ሰው እንዲጠቍም ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።
← Chapter 10
Chapter 12 →