bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Job 39
Job 39
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
“የበረሓ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋሊያ ስታምጥስ ተከታትለህ አይተሃል?
2
የእርግዝናቸው ወራት ምን ያህል እንደ ሆነ ትቈጥራለህን? የሚወልዱበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?
3
ተንበርክከው ይወልዳሉ፤ ከምጣቸውም ጣር ይገላገላሉ።
4
ግልገሎቻቸውም ይጠነክራሉ፤ በሜዳም ያድጋሉ፤ ተለይተው ይሄዳሉ፤ ወደ እነርሱም አይመለሱም።
5
“ለሜዳ አህያ ነጻነት የሰጠው ማን ነው? እስራቱንስ ማን ፈታለት?
6
ምድረ በዳውን መኖሪያው፣ የጨውንም ምድር ማደሪያው አድርጌ ሰጠሁት።
7
በከተማ ውካታ ይሥቃል፤ የነጂውንም ጩኸት አይሰማም።
8
በየተራራው ይሰማራል፤ ሐመልማሉንም ሁሉ ለማግኘት ይወጣል።
9
“ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን? በበረትህስ አጠገብ ያድራልን?
10
እንዲያርስልህ ልትጠምደው ትችላለህ? ወይስ እየተከተለህ ዕርሻህን ይጐለጕልልሃልን?
11
ጕልበቱ ብርቱ ስለሆነ ትተማመንበታለህ? ከባዱን ሥራህንስ ለእርሱ ትተዋለህ?
12
እህልህን እንዲሰበስብልህ፣ በዐውድማህም ላይ እንዲያከማችልህ ታምነዋለህን?
13
“ሰጎን ክንፎቿን በደስታ ታራግባለች፤ ነገር ግን እንደ ሽመላ ላባዎች ሊሆኑ አይችሉም።
14
ዕንቍላሏን መሬት ላይ ትጥላለች፤ እንዲሞቅም በአሸዋ ውስጥ ትተወዋለች።
15
እግር እንደሚሰብረው፤ የዱር አውሬም እንደሚረግጠው አታስብም።
16
የእርሷ እንዳልሆኑ ሁሉ በልጆቿ ትጨክናለች፤ ድካሟም በከንቱ ቢቀር ደንታ የላትም፤
17
እግዚአብሔር ጥበብ ነሥቷታልና፤ ማስተዋልንም አልሰጣትም።
18
ለመሸምጠጥም ክንፎቿን ስትዘረጋ፣ በፈረስና በጋላቢው ትሥቃለች።
19
“ለፈረስ ጕልበትን ትሰጠዋለህን? ዐንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን?
20
እንደ አንበጣ የምታስዘልለው አንተ ነህን? የማንኰራፋቱም ገናናነት አስፈሪ ነው።
21
በጕልበቱ እየተመካ በብርቱ ይጐደፍራል፤ ጦርነት ሊገጥም ይወጣል።
22
ያለ አንዳች ሥጋት፣ በፍርሀት ላይ ይሥቃል፤ ሰይፍ ቢመዘዝበትም ወደ ኋላ አይልም።
23
ከሚብረቀረቀው ጦርና ዐንካሴ ጋር፣ የፍላጻው ኰረጆ ጐኑ ላይ ይንኳኳል።
24
በወኔ መሬቱን እየጐደፈረ ወደ ፊት ይሸመጥጣል፤ የመለከት ድምፅ ሲሰማ ያቅበጠብጠዋል።
25
መለከቱ ሲያንባርቅ፣ ‘ዕሠይ’ ይላል፤ የአዛዦችን ጩኸትና የሰራዊቱን ውካታ፣ ጦርነትንም ከሩቅ ያሸትታል።
26
“ጭልፊት የሚበርረው፣ ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው፣ በአንተ ጥበብ ነውን?
27
ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው፣ ጎጆውንም በከፍታ ላይ የሚሠራው፣ በአንተ ትእዛዝ ነውን?
28
በገደል ላይ ይኖራል፤ በዚያም ያድራል፤ ምሽጉም የቋጥኝ ጫፍ ነው።
29
እዚያ ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፤ ዐይኑም ከሩቅ አጥርቶ ያያል።
30
ጫጩቶቹ ደም ይጠጣሉ፤ እርሱም በድን ካለበት አይታጣም።”
← Chapter 38
Chapter 40 →