bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Job 10
Job 10
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
“ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ፤ ስለዚህም ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቅቃለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።
2
እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፤ በምን ላይ እንዳልተስማማን ንገረኝ እንጂ አትፍረድብኝ።
3
የክፉዎችን ዕቅድ በደስታ እየተቀበልህ፣ እኔን ግን ስታስጨንቀኝ፣ የእጅህንም ሥራ ስታዋርድ ደስ ይልሃልን?
4
አንተ ዐይንህ የሥጋ ለባሽ ዐይን ነውን? ሟች የሆነ የሰው ልጅ እንደሚያይ ታያለህን?
5
ዘመንህ እንደ ሟች ሰው ዘመን ነውን? ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን?
6
ታዲያ፣ በደልን የምትፈላልግብኝ፣ ኀጢአቴንም የምትከታተለው ለምንድን ነው?
7
እኔ በደለኛ እንዳልሆንሁ፣ ከእጅህም ሊያስጥለኝ ማንም እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።
8
“እጅህ አበጀችኝ፤ ሠራችኝም፤ መልሰህ ደግሞ ታጠፋኛለህን?
9
እንደ ሸክላ እንዳበጀኸኝ ዐስብ፤ አሁን ደግሞ ወደ ትቢያ ትመልሰኛለህን?
10
እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን?
11
ቈዳና ሥጋ አለበስኸኝ፤ በዐጥንትና በጅማትም አገጣጥመህ ሠራኸኝ።
12
ሕይወትን ሰጠኸኝ፤ በጎነትንም አሳየኸኝ፤ እንክብካቤህም መንፈሴን ጠበቀ።
13
“ይህን ሁሉ ግን በልብህ ሸሸግህ፤ ነገሩ በዐሳብህ እንደ ነበር ዐውቃለሁ፤
14
ኀጢአትን ብሠራ ትመለከተኛለህ፤ መተላለፌንም ሳትቀጣ አታልፍም።
15
በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ ንጹሕ ብሆንም፣ ራሴን ቀና አላደርግም፤ ውርደትን ተከናንቤአለሁና፤ በመከራም ተዘፍቄአለሁ።
16
ራሴን ከፍ ከፍ ባደርግ፣ እንደ አንበሳ ታደባብኛለህ፤ አስፈሪ ኀይልህን ደጋግመህ ታሳየኛለህ፤
17
አዳዲስ ምስክሮችን ታመጣብኛለህ፤ ቍጣህንም በላዬ ትጨምራለህ፤ ሰራዊትህም ተከታትሎ ይመጣብኛል።
18
“ታዲያ ለምን ከማሕፀን አወጣኸኝ? ምነው ዐይን ሳያየኝ በሞትሁ ኖሮ!
19
ምነው ባልተፈጠርሁ! ወይም ከማሕፀን ቀጥታ ወደ መቃብር በወረድሁ!
20
ጥቂት የሆነው ዘመኔ እያለቀ አይደለምን? ከሥቃዬ ፋታ እንዳገኝ ተወት አድርገኝ፤
21
ወደማልመለስበት ስፍራ፣ ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ አገር ከመሄዴ በፊት፣
22
ብርሃኑ እንደ ጨለማ ወደ ሆነበት፣ የሞት ጥላ ወዳረበበበት፣ ሥርዐት የለሽ ወደ ሆነ ምድር፣ ድቅድቅ ጨለማ ወደ ሰፈነበት አገር ሳልሄድ ተወኝ።”
← Chapter 9
Chapter 11 →