bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Jeremiah 52
Jeremiah 52
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም አሚጣል ሲሆን፣ እርሷም የሊብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
2
ሴዴቅያስም ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
3
እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ይህን ሁሉ ያደረሰውንና በመጨረሻም ከፊቱ ያስወገዳቸው ከቍጣው የተነሣ ነበር። ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
4
ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ።
5
ከተማዪቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዘመነ መንግሥት ተከብባ ነበር።
6
በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን ዐጣ፤
7
የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።
8
የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት።
9
እርሱም በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ ተወሰደ፤ የባቢሎን ንጉሥ በዚያ ፈረደበት።
10
በሪብላም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በአባታቸው ፊት ዐረዳቸው፤ የይሁዳንም ባለሥልጣኖች ሁሉ ገደላቸው፤
11
የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ በናስ ሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ በዚያም እስከ ዕለተ ሞቱ በእስር ቤት አቈየው።
12
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር፤ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
13
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የንጉሡን ቤተ መንግሥት እንዲሁም በኢየሩሳሌም የነበሩትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ ሌሎች ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ።
14
በክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ሰራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር በሙሉ አፈረሱ።
15
የዘቦቹ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ፣ የእጅ ጥበብ ያላቸውንና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው።
16
ነገር ግን የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።
17
ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ገንዳ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ይዘው ሄዱ።
18
ከእነዚህም ሌላ ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ወጭቶቹን፣ ጭልፋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የናስ ዕቃዎች በሙሉ ወሰዱ።
19
የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ከንጹሕ ወርቅና ከንጹሕ ብር የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ጐድጓዳ ሳሕኖችን ጥናዎችን፣ ወጭቶችን፣ ምንቸቶችን፣ መቅረዞችን፣ ጭልፋዎችንና ለመጠጥ ቍርባን ማቅረቢያ የሚሆኑ ወጭቶችን ይዞ ሄደ።
20
ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ሚዛን ከሚችለው በላይ ነበር።
21
እያንዳንዱም ዐምድ ከፍታው ዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ።
22
በአንዱ ዐምድ ዐናት ላይ ያለው የናስ ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ሲሆን፣ ዙሪያውንም ሁሉ የሮማን ቅርጽ ባላቸው የናስ ጌጣጌጦች የተዋበ ነበር፤ ሌላውም ዐምድ የሮማኑን ጌጣጌጥ ጨምሮ ከዚሁ ጋር አንድ ዐይነት ነበር።
23
ዘጠና ስድስቱ ሮማኖች ከጐን በቀላሉ የሚታዩ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ በዙሪያው ካለው ጌጥ በላይ ያለው የሮማኖች ቍጥር አንድ መቶ ነበር።
24
የክብር ዘበኞቹ አዛዥ የካህናት አለቃ የነበረውን ሠራያን፣ ምክትሉንም ካህን ሶፎንያስንና ሦስቱን በር ጠባቂዎች አስሮ ወሰዳቸው፤
25
በከተማው ውስጥ ከቀሩትም ሕዝብ፣ የተዋጊዎቹ ኀላፊ የነበረውን መኰንን፣ ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች ከአገሬው ሕዝብ ወታደር የሚመለምለውን መኰንን ጸሓፊና በከተማው ውስጥ የተገኙትን ሌሎች ስድሳ ሰዎች ወሰደ።
26
የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው።
27
ንጉሡም በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ፈጃቸው። ይሁዳም በዚህ ሁኔታ ከምድሯ በምርኮ ተወሰደች።
28
ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰደው ሕዝብ ቍጥር እንደሚከተለው ነው፦ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ ሦስት ሺሕ ሃያ ሦስት አይሁድ፤
29
ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፤
30
ናቡከደነፆር በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ ሰባት መቶ አርባ አምስት አይሁድ ማርኮ ወስዷል። በአጠቃላይ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ሰዎች ነበሩ።
31
የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ ዮርማሮዴክ በባቢሎን ነገሠ፤ በዚሁ ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ አምስተኛው ቀን የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ዐሰበው፤ ከእስር ቤትም አወጣው፤
32
በመልካምም ቃል አናገረው፤ ከእርሱም ጋር በባቢሎን በምርኮ ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ባለ የክብር ቦታ አስቀመጠው።
33
ዮአኪንም እስር ቤት ለብሶት የነበረውን ልብሱን አውልቆ ጣለ፤ በቀረውም የሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከንጉሡ ማእድ ይበላ ነበር።
34
የባቢሎንም ንጉሥ፣ ዮአኪን እስኪሞት ድረስ፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ በየዕለቱ ቀለቡን ይሰጠው ነበር።
← Chapter 51