bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Jeremiah 29
Jeremiah 29
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ነቢዩ ኤርምያስ በምርኮ ተወስደው በሕይወት ለቀሩት ሽማግሌዎች፣ ለካህናቱ፣ ለነቢያቱና ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የላከው የደብዳቤ ቃል ይህ ነው፤
2
ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እቴጌዪቱ እናቱ፣ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፣ ዐናጺዎችና ብረት ቀጥቃጮች ተማርከው ከኢየሩሳሌም ከተወሰዱ በኋላ ነበር።
3
ደብዳቤውንም ከይሁዳ ንጉሥ ከሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር በተላኩት መልእክተኞች በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ላከው፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤
4
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤
5
“ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤
6
አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ።
7
ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።”
8
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤
9
በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር ።
10
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።
11
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር ፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጐዳ አይደለም።
12
እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።
13
እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤
14
እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር ፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር ፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”
15
እናንተም፣ “ እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያት አስነሥቶልናል” ትላላችሁ፤
16
እግዚአብሔር ግን በዳዊት ዙፋን ላይ ስለሚቀመጠው ንጉሥና ከእናንተ ጋር ተማርኮ ስላልሄደው ወገንህ በዚህ ከተማ ስለ ቀረው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ይላል፤
17
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን፣ ራብንና መቅሠፍትን እሰድድባቸዋለሁ፤ ከመበላሸቱ የተነሣም ሊበላ እንደማይቻል እንደ መጥፎ የበለስ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ።
18
በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት አሳድዳቸዋለሁ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉ አደርጋቸዋለሁ፤ በማሳድድባቸውም ሕዝቦች ዘንድ የርግማንና የድንጋጤ፣ የመሣቂያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ፤
19
በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ደጋግሜ የላክሁላቸውን ቃሌን አልሰሙምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “እናንተ ምርኮኞችም አልሰማችሁም” ይላል እግዚአብሔር ።
20
ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
21
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚነግሯችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፤ “እነዚህን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም ዐይናችሁ እያየ ይገድላቸዋል።
22
በእነርሱ ላይ ከደረሰው የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፣ ‘ እግዚአብሔር ፣ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግብህ’ ብለው ይራገማሉ፤
23
ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋር በማመንዘርና ያልነገርኋቸውን ቃል በስሜ በሐሰት በመናገር በእስራኤል ዘንድ በደል ፈጽመዋልና። ይህንም እኔ ዐውቃለሁ፤ ምስክር ነኝ” ይላል እግዚአብሔር ።
24
“ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤
25
‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌም ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ ለካህኑ ለመዕሤያ ልጅ ለሶፎንያስና ለሌሎችም ካህናት ሁሉ በገዛ ስምህ ደብዳቤዎችን ልከሃል፤ ለሶፎንያስም እንዲህ ብለሃል፤
26
“ በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ምትክ ካህን አድርጎ ሾሞሃል፤ ነቢይ ነኝ እያለ ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ያበደ ሰው እግሩን በግንድ፣ ዐንገቱን በሰንሰለት መቀፍደድ ይገባሃል።” ’
27
ታዲያ፣ ነቢይ ነኝ ባዩን የዓናቶቱን ኤርምያስን ለምን አልገሠጽኸውም?
28
ይህ ሰው፣ ‘የምርኮው ጊዜ ረዥም ስለሆነ፣ ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልትም ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ’ በማለት ወደ ባቢሎን መልእክት ልኮብናል።”
29
ካህኑ ሶፎንያስም ደብዳቤውን ለነቢዩ ኤርምያስ አነበበለት።
30
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
31
“ይህን መልእክት በምርኮ ላሉት ሁሉ እንዲህ ብለህ ላክ፤ ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችሁ፣ በሐሰት እንድትታመኑ አድርጓችኋልና፣
32
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ በእኔ ላይ ዐመፅን ተናግሯልና፣ በዚህ ሕዝብ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖረውም” ’ ይላል እግዚአብሔር ፤ ‘ለሕዝቤ የማደርገውንም መልካም ነገር አያይም።’ ”
← Chapter 28
Chapter 30 →