bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Jeremiah 13
Jeremiah 13
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር ፣ “ሄደህ ከተልባ እግር የተሠራ መቀነት ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅበት፤ ነገር ግን ውሃ አታስነካው” አለኝ።
2
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ መቀነቱን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁበት።
3
ለሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
4
“ገዝተህ የታጠቅህበትን መቀነት ይዘህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያም በዐለት ንቃቃት ውስጥ ሸሽገው።”
5
ስለዚህ እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ ሸሸግሁት።
6
ከብዙ ቀን በኋላም እግዚአብሔር ፣ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያ እንድትሸሽገው የነገርሁህን መቀነት አምጣ” አለኝ።
7
እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ፣ መታጠቂያውን ከሸሸግሁበት ቦታ ቈፍሬ አወጣሁ፤ መታጠቂያውም ተበላሽቶ፣ ከጥቅም ውጭም ሆኖ ነበር።
8
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
9
“ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳን ትዕቢትና የኢየሩሳሌምን እብሪት እንደዚሁ አጠፋለሁ።
10
ቃሌን መስማት እንቢ ብለው በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ ሊያመልኳቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን ጣዖቶች የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝቦች ከጥቅም ውጭ እንደ ሆነው እንደዚህ መቀነት ይበላሻሉ።
11
መቀነት በሰው ወገብ ላይ እንደሚታሰር፣ መላው የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከእኔ ጋር ተጣብቆ ለስሜ ምስጋናና ክብር፣ የእኔ ሕዝብ እንዲሆንልኝ አድርጌው ነበር፤ ሕዝቤ ግን አልሰማም’ ይላል እግዚአብሔር ።
12
“እንዲህ በላቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ ይሞላል’፤ እነርሱም፣ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ እንደሚሞላ እኛ አናውቅምን?’ ቢሉህ፣
13
እንዲህ በላቸው፤ ‘ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትን፣ ካህናትን፣ ነቢያትን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሁሉ ጨምሮ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ።
14
አንዱን ሰው ከሌላው ጋር፣ አባትንና ወንድ ልጅን እርስ በእርስ አጋጫለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር ፤ ያለ ሐዘኔታ፣ ያለ ምሕረትና ያለ ርኅራኄ አጠፋቸዋለሁ።’ ”
15
እግዚአብሔር ተናግሯልና፣ ስሙ፤ ልብ በሉ፤ ትዕቢተኛም አትሁኑ።
16
ጨለማን ሳያመጣ፣ በሚጨልሙትም ተራሮች ላይ፣ እግሮቻችሁ ሳይሰናከሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ፤ እርሱ ወደ ጨለማ ይለውጠዋል፤ ድቅድቅ ጨለማም ያደርገዋል።
17
ባትሰሙ ግን፣ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ፣ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔር መንጋ ተማርኳልና፣ ዐይኔ አምርሮ ያለቅሳል፤ እንባዬም እንደ ጐርፍ ይወርዳል።
18
ለንጉሡና ለእናቱ ለእቴጌዪቱ፣ “የክብር ዘውዳችሁ ከራሳችሁ ይወድቃልና፣ ከዙፋናችሁ ውረዱ” በላቸው።
19
በኔጌቭ ያሉ ከተሞች ይዘጋሉ፤ የሚከፍታቸውም አይኖርም። ይሁዳ ሁሉ ተማርኮ ይሄዳል፤ ሙሉ በሙሉም ይዘጋል።
20
ዐይኖቻችሁን ከፍታችሁ፣ ከሰሜን የሚመጡትን እዩ። ለአንቺ የተሰጠው መንጋ፣ የተመካሽባቸው በጎች የት አሉ?
21
ልዩ ወዳጆች እንዲሆኑሽ ያስተማርሻቸው፣ ባለ ሥልጣን ሲሆኑብሽ ምን ትያለሽ? እንደምትወልድ ሴት፣ ምጥ አይዝሽምን?
22
“ይህ ለምን ደረሰብኝ?” ብለሽ ራስሽን ብትጠይቂ፣ ልብስሽን ተገልበሽ የተገፈተርሽው፣ በሰውም እጅ የተንገላታሽው፣ ከኀጢአትሽ ብዛት የተነሣ ነው።
23
ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነብርስ ዝንጕርጕርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንት ክፉ ማድረግ የለመዳችሁትም፣ መልካም ማድረግ አትችሉም።
24
“የበረሓ ነፋስ ብትንትኑን እንደሚያወጣው ገለባ፣ እንዲሁ እበታትናችኋለሁ።
25
እኔን ረስተሽ፣ በከንቱ አማልክት ስለ ታመንሽ፣ ያወጅሁልሽ ድርሻሽ፣ ዕጣ ፈንታሽ ይህ ነው፤” ይላል እግዚአብሔር ፤
26
“ኀፍረትሽ እንዲገለጥ፣ ልብስሽን ፊትሽ ድረስ እገልባለሁ፤
27
በኰረብቶችና በሜዳዎች ላይ፣ አስጸያፊ ተግባርሽን፣ ምንዝርናሽንና ማሽካካትሽን፣ ኀፍረተ ቢስ ግልሙትናሽን አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ወዮልሽ፤ ከርኩሰትሽ የማትጸጂው እስከ መቼ ነው?”
← Chapter 12
Chapter 14 →