bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Isaiah 59
Isaiah 59
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እነሆ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም መስማት አልተሳናትም።
2
ነገር ግን በደላችሁ ከአምላካችሁ ለይቷችኋል፤ ኀጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፤ በዚህም ምክንያት አይሰማም።
3
እጆቻችሁ በደም፣ ጣቶቻችሁ በበደል ተነክረዋል፤ ከንፈሮቻችሁ ሐሰትን ተናገሩ፤ ምላሶቻችሁ ክፉ ነገርን አሰሙ።
4
ፍትሕን የሚጠራ ማንም የለም፤ ጕዳዩን በቅንነት የሚያቀርብ የለም፤ በከንቱ ነገር ታመኑ፤ ሐሰትን ተናገሩ፤ ሁከትን ፀነሱ፤ ክፋትንም ወለዱ።
5
የእባብ ዕንቍላል ታቀፉ፤ የሸረሪት ድር ዐደሩ፤ ዕንቍላሎቻቸውን የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤ አንዱ በተሰበረ ጊዜም እፉኝት ይወጣል።
6
ድሮቻቸው ልብስ አይሆኑም፤ በሚሠሩትም ሰውነታቸውን መሸፈን አይችሉም፤ ሥራቸው ክፉ ነው፤ እጃቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞላ ነው።
7
እግሮቻቸው ወደ ኀጢአት ይሮጣሉ፤ ንጹሕ ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ የሚያስቡት ክፉ ሐሳብ ነው፤ ማጥፋትና ማፈራረስም የመንገዳቸው ምልክት ነው።
8
የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ በጐዳናቸውም ፍትሕ የለም፤ መንገዳቸውን ጠማማ አድርገውታል፤ በዚያም የሚሄድ ሰላም አያገኝም።
9
ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቋል፤ ጽድቅም ወደ እኛ አይመጣም፤ ብርሃንን ፈለግን፤ ነገር ግን ሁሉ ጨለማ ነው፤ የብርሃንን ጸዳል ፈለግን፤ የምንሄደው ግን በድንግዝግዝታ ነው።
10
በቅጥሩ ላይ እንደ ዕውር ተደናበርን፤ አካሄዳችንም ዐይን እንደሌላቸው በዳበሳ ሆነ፤ ጀንበር በምትጠልቅበት ጊዜ እንደሚሆነው በእኩለ ቀን ተደናበርን፤ በብርቱዎች መካከልም እንደ ሙታን ሆንን።
11
ሁላችን እንደ ድቦች እናላዝናለን፤ እንደ ርግቦችም በመቃተት እንጮኻለን፤ ፍትሕን ፈለግን፤ ግን አላገኘንም፤ ትድግናን ፈለግን፤ ነገር ግን ከእኛ ርቋል።
12
በደላችን በፊትህ በዝቷል፤ ኀጢአታችን መስክሮብናል፤ በደላችን ከእኛ አልተለየም፤ ዐመፀኝነታችንንም እናውቃለን።
13
በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ሐሰት ተናግረናል፤ አምላካችንን ከመከተል ዘወር ብለናል፤ ዐመፃንና ግፍን አውርተናል፤ ልባችን የፀነሰውን ውሸት ተናግረናል።
14
ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቋል፤ ጽድቅም በሩቁ ቆሟል፤ እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሏል፤ ቅንነትም መግባት አልቻለም።
15
እውነት የትም ቦታ አይገኝም፤ ከክፋት የሚርቅ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። እግዚአብሔር ተመለከተ፤ ፍትሕ በመታጣቱም ዐዘነ።
16
ማንም እንደሌለ አየ፤ ወደ እርሱ የሚማልድ ባለመኖሩ ተገረመ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ ድነት አመጣለት፤ የራሱም ጽድቅ ደግፎ ያዘው።
17
ጽድቅን እንደ ጥሩር አጠለቀ፤ የድነትን ቍር በራሱ ላይ ደፋ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤ መጐናጸፊያ እንደሚደረብም ቅናትን ደረበ።
18
እንደ ሥራቸው መጠን፣ ቍጣን ለባላጋራዎቹ፣ ፍዳን ለጠላቶቹ፣ እንደዚሁ ይከፍላቸዋል፤ ለደሴቶችም የእጃቸውን ይሰጣቸዋል።
19
በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም ይፈራሉ፤ በፀሓይ መውጫ ያሉት ለክብሩ ይገዛሉ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እንደ ተቋተ፣ እንደ ተከማቸም ጐርፍ ይመጣልና።
20
“አዳኝ ወደ ጽዮን፣ ኀጢአታቸውንም ወደ ተናዘዙት ወደ ያዕቆብ ቤት ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር።
21
“በእኔ በኩል፣ ከእነርሱ ጋር ያለኝ ቃል ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር ፤ “በአንተም ላይ ያለው መንፈሴ፣ በአፍህ ያስቀመጥሁት ቃሌ ከአፍህ፣ ከልጆችህ አፍ፣ ከዘር ዘሮቻቸውም አፍ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም አይለይም” ይላል እግዚአብሔር ።
← Chapter 58
Chapter 60 →