bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Isaiah 42
Isaiah 42
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
“ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ ምርጤ ይህ ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል።
2
አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም።
3
የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል።
4
ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣ አይደክምም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።”
5
ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣ ለሕዝቧ እስትንፋስን፣ ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
6
“እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ።
7
የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ።
8
“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።
9
እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሟል፤ እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ፤ ከመብቀሉም በፊት፣ ለእናንተ አስታውቃለሁ።”
10
እናንት ወደ ባሕር የምትወርዱ፣ በዚያም ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በዚያ የምትኖሩ በሙሉ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድር ዳርቻም ምስጋናውን ዘምሩ።
11
ምድረ በዳውና ከተሞቹ ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤ ቄዳር ያለችበት መንደር ደስ ይበለው፤ የሴላ ሕዝቦች በደስታ ይዘምሩ፤ ከተራሮችም ራስ ላይ ይጩኹ።
12
ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ።
13
እግዚአብሔር እንደ ኀያል ሰው ይዘምታል፤ እንደ ተዋጊ በወኔ ይነሣል፤ የቀረርቶ ጩኸት ያሰማል፤ ጠላቶቹንም ድል ያደርጋል።
14
“ለረዥም ጊዜ ዝም አልሁ፤ ጸጥ አልሁ፤ ራሴንም ገታሁ፤ አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣ እጮኻለሁ፤ ቍና ቍና እቃትታለሁ፤ እተነፍሳለሁ።
15
ተራራውንና ኰረብታውን አፈርሳለሁ፤ ዕፀዋቱን ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዙንም ደሴት አደርጋለሁ፤ ኵሬውን አደርቃለሁ።
16
ዕውሮችን በማያወቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ። ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ። ይህን አደርጋለሁ፤ አልተዋቸውም።
17
በጣዖት የሚታመኑ ግን፣ ምስሎችን፣ ‘አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ፣ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመው ይዋረዳሉም።
18
“እናንት ደንቈሮዎች ስሙ፤ እናንት ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም።
19
አገልጋዬ እንጂ፣ ሌላ ዕውር ማን አለ? ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ማን ደንቈሮ አለ? ለእኔ ታማኝ እንደ ሆነ ሰው የታወረ፣ እንደ እግዚአብሔርስ አገልጋይ ዕውር ማነው?
20
ብዙ ነገርን አያችሁ፤ ነገር ግን አላስተዋላችሁም፤ ጆሯችሁ ክፍት ነው፤ ነገር ግን ምንም አትሰሙም።”
21
እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሲል፣ ሕጉን ታላቅና የተከበረ በማድረግ ደስ አለው።
22
ይህ ሕዝብ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ፣ በጕድጓድ ውስጥ የተጠመደበት፣ በወህኒ ቤት የተዘጋበት ነው፤ ተበዝብዘዋል፣ የሚያድናቸውም የለም፤ ተማርከዋል፣ “መልሷቸው” የሚልም የለም።
23
ከእናንተ ይህን የሚሰማ፣ ለሚመጣውም ጊዜ አስተውሎ የሚያደምጥ ማነው?
24
ያዕቆብን ለዝርፊያ፣ እስራኤልን ለምርኮ የዳረገ ማነው? በኀጢአት የበደልነው፣ እግዚአብሔር አይደለምን? መንገዱን ለመከተል፣ ለሕጉም መታዘዝ አልፈለጉምና።
25
ስለዚህ የሚነድድ ቍጣውን፣ የጦርነትንም መዓት አፈሰሰባቸው፤ በእሳት ነበልባል ከበባቸው፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤ አቃጠላቸው፤ እነርሱ ግን ልብ አላሉም።
← Chapter 41
Chapter 43 →