bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Isaiah 34
Isaiah 34
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እናንት አሕዛብ ሆይ፤ ኑ አድምጡም፤ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አስተውሉ። ምድርና በውስጧ ያለ ሁሉ፣ ዓለምና ከእርሷ የሚበቅል ሁሉ ይስማ።
2
እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ ተቈጥቷል፤ ቍጣውም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ ያጠፋቸዋል ፤ ለዕርድም አሳልፎ ይሰጣቸዋል።
3
ከእነርሱም የተገደሉት ወደ ውጭ ይጣላሉ፤ ሬሳቸው ይከረፋል፤ ተራሮችም ደም በደም ይሆናሉ።
4
የሰማይ ከዋክብት ሁሉ ይሟሽሻሉ፤ ሰማይ እንደ ብራና ይጠቀለላል፤ የከዋክብት ሰራዊት ሁሉ፣ ጠውልጎ እንደ ረገፈ የወይን ቅጠል፣ ደርቆም እንደ ወደቀ የበለስ ቅጠል ይሆናሉ።
5
ሰይፌ በሰማያት እስኪበቃት ጠጥታለች፤ እነሆ፤ ወደ ኤዶም፣ ፈጽሞ ወዳጠፋሁት ሕዝብ ለፍርድ ወርዳለች።
6
የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተነክራለች፤ ሥብ ጠግባለች፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም፣ በአውራም በግ ኵላሊት ሥብ ተሸፍናለች። እግዚአብሔር በባሶራ ከተማ መሥዋዕት፣ በኤዶምም ታላቅ ዕርድ አዘጋጅቷልና።
7
ጐሽ አብሯቸው፣ ኮርማም ከወይፈን ጋር ይወድቃል፤ ምድራቸው በደም ትርሳለች፤ ዐፈራቸውም ሥብ በሥብ ይሆናል።
8
እግዚአብሔር የበቀል ቀን፣ ስለ ጽዮንም የሚሟገትበት ዓመት አለውና።
9
የኤዶም ምንጮች ሬንጅ፣ ዐፈሯ የሚቃጠል ድኝ፣ ምድሯም የሚንበለበል ዝፍት ይሆናል።
10
እሳቷ ሌሊትና ቀን አይጠፋም፤ ጢሷም ለዘላለም ይትጐለጐላል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድ ባድማ ትሆናለች፤ ማንም በዚያ ዳግም አያልፍም።
11
ጭልፊትና ጃርት ይወርሷታል፤ ጕጕትና ቍራም ጐጆ ይሠሩባታል። እግዚአብሔር በኤዶም ላይ፣ የመፈራረሷን ገመድ፣ የመጥፊያዋንም ቱንቢ ይዘረጋል።
12
መሳፍንቷም መንግሥት ተብለው ለመጠራት የሚያስችላቸው ነገር አይኖራቸውም፤ አለቆቿም በሙሉ ጥርግ ብለው ይጠፋሉ።
13
በቅጥር የተመሸጉ ከተሞቿን እሾኽ፣ ምሽጎቹንም ሳማና አሜከላ ይወርሷቸዋል፤ የቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የጕጕቶችም መኖሪያ ትሆናለች።
14
የምድረ በዳ አራዊት ከጅቦች ጋር አብረው ይሆናሉ፤ በበረሓ ፍየል የሚመሰሉ አጋንንትም እርስ በእርስ ይጠራራሉ፤ የሌሊት ፍጥረታት ማረፊያቸውን በዚያ ያደርጋሉ፤ ለራሳቸውም የማረፊያ ቦታ ያገኛሉ።
15
ጕጕት በዚያ ጐጆ ሠርታ ዕንቍላል ትጥላለች፤ ትቀፈቅፋለች፤ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ትታቀፋቸዋለች፤ ጭላቶችም ጥንድ ጥንድ ሆነው፣ ለርቢ በዚያ ይሰበሰባሉ።
16
በእግዚአብሔር መጽሐፍ እንዲህ የሚለውን ተመልከቱ፤ አንብቡም፤ ከእነዚህ አንዱ አይጐድልም፤ እያንዳንዷም አጣማጇን አታጣም፤ ይህ ትእዛዝ ከአፉ ወጥቷል፤ መንፈሱ በአንድ ላይ ይሰበስባቸዋልና።
17
ድርሻ ድርሻቸውን ይመድብላቸዋል፤ እጁም ለክታ ታካፍላቸዋለች። ለዘላለም የእነርሱ ትሆናለች፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ይኖሩባታል።
← Chapter 33
Chapter 35 →