bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Isaiah 31
Isaiah 31
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው!
2
እርሱም ግን ጠቢብ ነው፤ ጥፋትን ያመጣል፤ ቃሉን አያጥፍም። በክፉ አድራጊዎች ቤት ላይ፣ በደለኞችንም በሚረዱ ላይ ይነሣል።
3
ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን ሲዘረጋ፣ ርዳታ ሰጪው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።
4
እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፤ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል የሰበረውን ይዞ ሲያገሣ፣ ብዙ እረኞች ተጠራርተው ሲመጡበት፣ ጩኸታቸው እንደማያስፈራው፣ በድምፃቸውም እንደማይታወክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፣ በጽዮን ተራራና በከፍታዎቿ ላይ ለውጊያ እንዲሁ ይወርዳል።
5
በዐናት ላይ እንደሚያንዣብቡ ወፎች፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲሁ ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፤ ይታደጋታል፤ በላይዋ ያልፋል፤ ያድናታልም።”
6
እናንተ እስራኤላውያን ሆይ፤ እጅግ ወዳመፃችሁበት ወደ እርሱ ተመለሱ።
7
በዚያን ቀን በኀጢአት የተሞላ እጃችሁ የሠራቸውን የወርቅና የብር ጣዖቶች ሁላችሁም ትጥላላችሁና።
8
“አሦር የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፤ የሥጋ ለባሽ ያልሆነም ሰይፍ ይበላዋል። ከሰይፍ ፊት ይሸሻል፤ ጕልማሶቹም የግዳጅ ሥራ ይሠራሉ።
9
ጠንካራ ምሽጉ በሽብር ምክንያት ይወድቃል፤ መሪዎቹም የጦር ዐርማ ሲያዩ በድንጋጤ ይዋጣሉ” ይላል እሳቱ በጽዮን፣ ማንደጃውም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር ።
← Chapter 30
Chapter 32 →