bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Isaiah 14
Isaiah 14
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤ እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤ በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል። መጻተኞች አብረዋቸው ይኖራሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተባበራሉ።
2
አሕዛብም ይወስዷቸዋል፤ ወደ ገዛ ስፍራቸውም ይመልሷቸዋል። የእስራኤል ቤት አሕዛብን ርስት ያደርጓቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ምድር ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች አድርገው ይገዟቸዋል፤ የማረኳቸውን ይማርኳቸዋል፤ የጨቈኗቸውንም ይገዟቸዋል።
3
እግዚአብሔር ከሥቃይህ፣ ከመከራህና ከጽኑ ባርነትህ ባሳረፈህ ቀን፣
4
በባቢሎን ንጉሥ ላይ ትሣለቃለህ፤ እንዲህም ትላለህ፤ ጨቋኙ እንዴት አበቃለት! አስገባሪነቱስ እንዴት አከተመ!
5
እግዚአብሔር የክፉዎችን ዘንግ፣ የገዦችንም በትረ መንግሥት ሰብሯል፤
6
ሕዝቦችን በማያቋርጥ ቍጣ የመታውን፣ ያለ ርኅራኄ እያሳደደ የቀጠቀጠውን ሰብሯል።
7
ምድር ሁሉ ሰላምና ዕረፍት አግኝታለች፤ የደስታም ዝማሬ ታስተጋባለች።
8
ጥድና የሊባኖስ ዝግባ እንኳ ደስ ብሏቸው፣ “አንተም ወደቅህ፤ ዕንጨት ቈራጭም መጥረቢያ አላነሣብንም” አሉ።
9
በመጣህ ጊዜ ሲኦል ልትቀበልህ ተነሣሥታለች፤ ይቀበሉህም ዘንድ የሙታንን መናፍስት፣ በዓለም ገዥ የነበሩትን ሁሉ ቀስቅሳለች፤ በአሕዛብ ላይ የነገሡትን ነገሥታት ከዙፋናቸው አውርዳለች።
10
እነርሱ ሁሉ ይመልሱልሃል፤ እንዲህም ይሉሃል፤ “አንተም እንደ እኛ ደከምህ፤ እንደ እኛም ሆንህ።”
11
ክብርህ፣ ከነበገና ድምፁ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ብሎች ከበታችህ ተነጥፈዋል፤ ትሎችም መደረቢያህ ይሆናሉ።
12
አንተ የንጋት ልጅ፣ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፤ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አንተ ቀድሞ መንግሥታትን ያዋረድህ፣ እንዴት ወደ ምድር ተጣልህ!
13
በልብህም እንዲህ አልህ፤ “ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤ በተራራው መሰብሰቢያ፣ በተቀደሰውም ተራራ ከፍታ ላይ በዙፋኔ እቀመጣለሁ፤
14
ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።”
15
ነገር ግን ወደ ሲኦል፣ ወደ ጥልቁም ጕድጓድ ወርደሃል።
16
የሚያዩህም አትኵረው እየተመለከቱህ፣ በመገረም ስለ አንተ እንዲህ ይላሉ፤ “ያ ምድርን ያናወጠ፣ መንግሥታትን ያንቀጠቀጠ፣ ይህ ሰው ነውን?
17
ዓለምን ምድረ በዳ ያደረገ፤ ከተሞችን ያፈራረሰ፣ ምርኮኞቹንም ወደ አገራቸው እንዳይሄዱ የከለከለ ይህ ነውን?”
18
የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በክብር አንቀላፍተዋል፤ በየመቃብራቸው ዐርፈዋል።
19
አንተ ግን እንደማይፈለግ ቅርንጫፍ፣ ከመቃብር ወጥተህ ተጥለሃል፤ በሰይፍ በተወጉት፣ ወደ ጥልቁ ድንጋዮች በወረዱት፣ በተገደሉትም ተሸፍነሃል፤ እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል።
20
ከእነርሱ ጋር በመቃብር አትሆንም፤ ምድርህን አጥፍተሃልና፤ ሕዝብህንም ፈጅተሃልና። የክፉ አድራጊዎች ዘር ፈጽሞ አይታወስም።
21
ተነሥተው ምድርን እንዳይወርሱ፣ ዓለምንም በከተሞቻቸው እንዳይሞሉ፣ ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት፣ ወንድ ልጆቹ የሚታረዱበትን ስፍራ አዘጋጁ።
22
“በእነርሱ ላይ እነሣለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ። “ስሟንና ትሩፋኖቿን፣ ዘሯንና ትውልዷን ከባቢሎን እቈርጣለሁ” ይላል እግዚአብሔር ።
23
“የጃርት መኖሪያ፣ ረግረጋማ ቦታ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ።
24
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሏል፤ “እንደ ዐቀድሁት በርግጥ ይከናወናል፤ እንደ አሰብሁትም ይሆናል።
25
አሦርን በምድሬ ላይ አደቅቃለሁ፤ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩ ከሕዝቤ ላይ ይነሣል፤ ሸክሙም ከትከሻቸው ላይ ይወርዳል።”
26
ለምድር ሁሉ የታሰበው ዕቅድ ይህ ነው፤ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋው እጅ ይኸው ነው።
27
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አስቧል፤ ማንስ ያግደዋል? እጁም ተዘርግቷል? ማንስ ይመልሰዋል?
28
ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት እንዲህ የሚል ንግር መጣ፤
29
“እናንት ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ የመታችሁ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁ ደስ አይበላችሁ፤ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፤ ፍሬውም ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ ይሆናል።
30
ከድኻም ድኻ የሆኑት መሰማሪያ ያገኛሉ፤ ችግረኞችም ተዝናንተው ይተኛሉ፤ ሥርህን ግን በራብ እገድላለሁ፤ ትሩፋንህንም እፈጃለሁ።
31
“በር ሆይ፤ ዋይ በል! ከተማ ሆይ፤ ጩኽ! ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ ሁላችሁም በፍርሀት ቅለጡ! ጢስ ከሰሜን መጥቶብሃል፤ ከሰልፉ ተነጥሎ የሚቀር የለምና።
32
ከዚያ ሕዝብ ለሚመጡ መልእክተኞች ምን መልስ ይሰጣል? መልሱ፣ ‘ እግዚአብሔር ጽዮንን መሥርቷል፤ መከራን የተቀበለው ሕዝብም፣ በእርሷ ውስጥ መጠጊያን አግኝቷል’ የሚል ነው።”
← Chapter 13
Chapter 15 →