bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Hosea 9
Hosea 9
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እስራኤል ሆይ፤ ደስ አይበልሽ፤ እንደ ሌሎችም ሕዝቦች ሐሤት አታድርጊ፤ ለአምላክሽ ታማኝ አልሆንሽምና፤ በየእህል ዐውድማውም ላይ፣ ለጋለሞታ የሚከፈለውን ዋጋ ወድደሻል።
2
የእህል ዐውድማዎችና የወይን መጭመቂያዎች ሕዝቡን አይመግቡም፤ አዲሱም የወይን ጠጅ ይጐድልባቸዋል።
3
በእግዚአብሔር ምድር አይቀመጡም፤ ኤፍሬም ወደ ግብፅ ይመለሳል፤ የረከሰውንም ምግብ በአሦር ይበላል።
4
የወይን ጠጅን ቍርባን ለእግዚአብሔር አያፈስሱም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ እንዲህ ዐይነቱ መሥዋዕት ለእነርሱ የሐዘንተኞች እንጀራ ይሆንባቸዋል፤ የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ። ይህ ምግብ ለገዛ ራሳቸው ይሆናል፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ አይገባም።
5
በእግዚአብሔር የበዓል ቀናት፣ በዓመት በዓሎቻችሁም ቀን ምን ታደርጋላችሁ?
6
ከጥፋት ቢያመልጡም እንኳ፣ ግብፅ ትሰበስባቸዋለች፤ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች። የብር ሀብታቸውን ዳዋ ያለብሰዋል፤ ድንኳኖቻቸውንም እሾኽ ይወርሳቸዋል።
7
የቅጣት ቀን መጥቷል፤ የፍርድም ቀን ቀርቧል፤ እስራኤልም ይህን ይወቅ! ኀጢአታችሁ ብዙ፣ ጠላትነታችሁም ታላቅ ስለሆነ፣ ነቢዩ እንደ ሞኝ፣ መንፈሳዊውም ሰው እንደ እብድ ተቈጥሯል።
8
ነቢዩ ከአምላኬ ጋር ሆኖ፣ የኤፍሬም ጠባቂ ነው፤ ዳሩ ግን በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ፣ በአምላኩም ቤት ጠላትነት ይጠብቀዋል።
9
በጊብዓ እንደ ነበረው፣ በርኩሰት ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።
10
“እስራኤልን ማግኘቴ፣ የወይንን ፍሬ በምድረ በዳ የማግኘት ያህል ነበር፤ አባቶቻችሁንም ማየቴ፣ የመጀመሪያውን የበለስ ፍሬ የማየት ያህል ነበር፤ ወደ ብዔልፌጎር በመጡ ጊዜ ግን፣ ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤ እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ።
11
የኤፍሬም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድ፣ ማርገዝና መፅነስ የለም።
12
ልጆችን ቢያሳድጉ እንኳ፣ ልጅ አልባ እስኪሆኑ ድረስ እነጥቃቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ ወዮ ለእነርሱ!
13
ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ፣ በመልካም ስፍራ ተተክሎ አየሁት፤ አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን፣ ለነፍሰ ገዳዮች አሳልፎ ይሰጣል።”
14
እግዚአብሔር ሆይ፤ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፉ ማሕፀኖችን፣ የደረቁ ጡቶችን ስጣቸው።
15
“በጌልገላ ካደረጉት ክፋታቸው ሁሉ የተነሣ፣ እኔ በዚያ ጠላኋቸው፤ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አልወድዳቸውም፤ መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ናቸው።
16
ኤፍሬም ተመታ፤ ሥራቸው ደረቀ፤ ፍሬም አያፈሩም፤ ልጆች ቢወልዱም እንኳ፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።”
17
ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተንከራታች ይሆናሉ።
← Chapter 8
Chapter 10 →