bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Genesis 49
Genesis 49
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹን ሁሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባችሁ እነግራችሁ ዘንድ ተሰብሰቡ፤
2
“እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ ተሰብሰቡና ስሙ፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ፤
3
“ሮቤል፣ አንተ የበኵር ልጄ ነህ፤ ኀይሌና የጕብዝናዬም መጀመሪያ፤ በክብር ትልቃለህ፤ በኀይልም ትበልጣለህ።
4
እንደ ውሃ የዋለልህ ነህና እልቅና አይኖርህም፤ የአባትህን መኝታ ደፍረሃል፤ ምንጣፌንም አርክሰሃል።
5
“ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች፣ ሰይፎቻቸው የዐመፅ መሣሪያዎች ናቸው።
6
ወደ ሸንጓቸው አልግባ፤ ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፤ በቍጣ ተነሣሥተው ሰዎችን ገድለዋል፤ የበሬዎችንም ቋንጃ እንዳሻቸው ቈራርጠዋል።
7
እጅግ አስፈሪ የሆነ ቍጣቸው፣ ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤ በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፤ በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ።
8
“ይሁዳ፣ ወንድሞችህ ይወድሱሃል፤ እጅህም የጠላቶችህን ዐንገት ዐንቆ ይይዛል፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይሰግዱልሃል።
9
አንተ የአንበሳ ደቦል ይሁዳ፤ ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣ እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ በምድርም ላይ ይተኛል፤ እንደ እንስት አንበሳም ያደባል፤ ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል?
10
በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል። ገዥነት የሚገባው እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል።
11
አህያውን በወይን ግንድ፣ ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጐናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል።
12
ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።
13
“ዛብሎን፣ በባሕር ዳር ይኖራል፤ የመርከቦች መጠጊያም ይሆናል፤ ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል።
14
“ይሳኮር፣ በጭነት መካከል የሚተኛ ዐጥንተ ብርቱ አህያ ነው።
15
ማረፊያ ቦታው መልካም፣ ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣ ትከሻውን ለሸክም ያመቻቻል፤ ተገድዶም ያገለግላል።
16
“ዳን፣ ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ፣ በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።
17
ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣ የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣ የፈረሱን ሰኰና ይነክሳል።
18
“ እግዚአብሔር ሆይ (ያህዌ) ፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።
19
“ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።
20
“አሴር ማእደ ሰፊ ይሆናል፤ ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።
21
“ንፍታሌም ነጻ እንደ ተለቀቀች፣ የሚያማምሩም ግልገሎች እንደምትወልድ ሚዳቋ ነው።
22
“ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣ በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው። ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።
23
ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤ በጥላቻም ነደፉት።
24
ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣ እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤ ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ።
25
አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣ ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።
26
ከጥንት ተራሮች በረከት፣ ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣ የአባትህ በረከት ይበልጣል። ይህ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።
27
“ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።”
28
እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው።
29
ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሷል፤ በኬጢያዊው በኤፍሮን ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤
30
ይህ በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ ውስጥ ያለው ዋሻ፣ የመቃብር ቦታ እንዲሆን አብርሃም ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ ከነዕርሻ ቦታው የገዛው ነው።
31
በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤
32
እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው። ዕርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን ላይ ነው።”
33
ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ፣ እግሮቹን በዐልጋው ላይ ሰብስቦ፣ የመጨረሻ ትንፋሹን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።
← Chapter 48
Chapter 50 →