bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Genesis 30
Genesis 30
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ስለዚህ ያዕቆብን፣ “ልጅ ስጠኝ፤ አለዚያ እሞታለሁ” አለችው።
2
ያዕቆብም ራሔልን ተቈጥቶ “እኔ እንዳትወልጂ ያደረገሽን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መሰልኹሽን?” አላት።
3
እርሷም፣ “እነሆ፤ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በእርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከእርሷ ጋር ተኛ” አለችው።
4
ስለዚህም አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም አብሯት ተኛ፤
5
እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።
6
ራሔልም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፈርዶልኛል፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ አወጣችለት።
7
የራሔል አገልጋይ ባላ እንደ ገና ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች።
8
ራሔልም፣ “እኅቴን ብርቱ ትግል ገጥሜ አሸነፍሁ” አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ አወጣችለት።
9
ልያም ልጅ መውለድ ማቆሟን እንደ ተረዳች፣ አገልጋይዋን ዘለፋን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው።
10
የልያ አገልጋይ ዘለፋም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤
11
ልያም፣ “ምን ዐይነት መታደል ነው” አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ አወጣችለት።
12
የልያም አገልጋይ ዘለፋ፤ ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤
13
ልያም፣ “ምንኛ ደስተኛ ሆንሁ ከእንግዲህ ሴቶች ደስተኛዋ ይሉኛል” አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ አወጣችለት።
14
ስንዴ በሚታጨድበት ወቅት፣ ሮቤል ወደ ሜዳ ወጣ፤ እንኮይም አግኝቶ ለእናቱ ለልያ አመጣላት። ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት።
15
ልያም፣ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። ራሔልም፣ “ስለ ልጅሽ እንኮይ ዛሬ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት።
16
በዚያች ምሽት ያዕቆብ ከዕርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለ ተከራየሁህ የዛሬው ዐዳርህ ከእኔ ጋር ነው” አለችው፤ ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከእርሷ ጋር ዐደረ።
17
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የልያን ጸሎት ሰማ፤ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም አምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች።
18
ልያም፣ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ክሶኛል” አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ አወጣችለት።
19
ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች።
20
እርሷም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በከበረ ስጦታ ዐድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት፣ ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል”። አለች፤ ስሙንም ዛብሎን አለችው።
21
ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ዲና አለቻት።
22
እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ራሔልን ዐሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ ማሕፀኗን ከፈተላት።
23
ከዚያም ፀንሳ፣ ወንድ ልጅ ወለደችና “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤
24
ስሙንም፣ “ እግዚአብሔር (ይህዌ) ሌላ ወንድ ልጅ ጨምሮ ይስጠኝ” ስትል፣ ዮሴፍ አለችው።
25
ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፤ “ወደ ገዛ ቤቴ፣ ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ፤
26
የድካሜ ዋጋ የሆኑትን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ይዤአቸው ልሂድ፤ መቼም የቱን ያህል እንዳገለገልሁህ ታውቃለህ” አለው።
27
ላባም እንዲህ አለው፤ “በጎ ፈቃድህ ቢሆን፣ እባክህ እዚሁ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርም (ያህዌ) በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ በንግርት ተረድቻለሁ፤
28
ይልቅስ ይገባኛል የምትለውን ደመወዝ ንገረኝና እከፍልሃለሁ።”
29
ያዕቆብም እንዲህ አለው፤ “መቼም እንዴት እንዳገለገልሁህ፣ ከብቶችህ በእኔ ጥበቃ ምን ያህል እንደ ተመቻቸው አንተ ታውቃለህ።
30
እኔ ከመምጣቴ በፊት ጥቂት የነበረው ሀብትህ ዛሬ ተትረፍርፏል፣ በተሰማራሁበት ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) በረከቱን አብዝቶልሃል። ታዲያ፣ ስለ ራሴ ቤት የማስበው መቼ ነው?”
31
ላባም፣ “ታዲያ ምን ልስጥህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ምንም አትስጠኝ፤ ነገር ግን የምጠይቅህን አንዲት ነገር ብቻ ብታደርግልኝ ከብቶችህን ማገዴን እቀጥላለሁ፤
32
በመንጎቹ መካከል ዛሬ ልዘዋወርና ከበጎቹ መካከል ዝንጕርጕር የሆኑትን፣ ነቍጣ ያለባቸውንና ጥቋቁሮቹን እንዲሁም ከፍየሎቹ ነቍጣ ያለባቸውንና ዝንጕርጕሮቹን ልምረጥ፤ እነዚህ ደሞዜ ይሁኑ።
33
ወደ ፊት ደሞዜን ለመቈጣጠር በምትመጣበት ጊዜ ታማኝነቴ ይታወቃል፤ በመንጎቼ መካከል ዝንጕርጕር ወይም ነቍጣ የሌለበት ፍየል ወይም ጥቁር ያልሆነ ቢገኝ ያ እንደ ተሰረቀ ይቈጠር።”
34
ላባም፣ “እሺ፣ ይሁን፤ ባልኸው ተስማምቼአለሁ” አለው።
35
ነገር ግን በዚያኑ ዕለት ከተባዕት ፍየሎች ሽመልመሌ የሆኑትን ወይም ነቍጣ ያለባቸውን ሁሉ፣ እንዲሁም ከእንስት ፍየሎች ነቍጣ ያለባቸውን ዝንጕርጕር የሆኑትን ሁሉ፣ ማንኛውንም ነጭ ያለበትን ሁሉ መረጠ፤ ደግሞም ጥቋቁር የሆኑትንም በጎች ሁሉ ለየና ወንዶች ልጆቹን አስጠበቃቸው።
36
ከዚያም በእርሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ማገዱን ቀጠለ።
37
ነገር ግን ያዕቆብ እርጥብ የልብን፣ የለውዝንና የኤርሞን በትሮች ወሰደ፤ ቅርፊታቸውንም በቀጭን ልጦ እያነሣ የበትሮቹ ግንድ ነጩ እንዲታይ፣ ሽመልመሌ መልክ እንዲኖራቸው አደረገ።
38
የላጣቸውንም በትሮች መንጎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው በማጠጫ ገንዳዎቹ ሁሉ አስቀመጠ። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣
39
በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ።
40
ያዕቆብ ግልገሎቹን ለብቻ ለያቸው፤ የቀሩትንም የላባ መንጎች ሽመልመሌና ጥቋቁር በሆኑት ትይዩ አቆማቸው፤ በዚህም መሠረት የራሱ መንጋ ከላባ መንጋ ጋር እንዳይቀላቀል ለብቻ ለየ።
41
ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠበጡበት ጊዜ፣ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎቹ ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤
42
ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን፣ በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ።
43
በዚህም ሁኔታ ይህ ሰው እጅግ ባለጠጋ ሆነ፤ የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት ሆነ።
← Chapter 29
Chapter 31 →