bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Genesis 28
Genesis 28
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ይስሐቅ ያዕቆብን አስጠርቶ ከመረቀው በኋላ፣ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ምንም ቢሆን ከነዓናዊት ሴት አታግባ።
2
አሁኑኑ ተነሥተህ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ እዚያም ከአጎትህ ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዲቷን አግባ።
3
ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ይባርክህ፤ ብዙ ሕዝብ እስክትሆን ድረስ ልጆች አፍራ፤ ዘርህን ያብዛው።
4
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ።”
5
ይስሐቅም ያዕቆብን በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ወደ ሆነው ወደ ሶርያዊው የባቱኤል ልጅ ወደ ላባ ላከው።
6
ዔሳው፣ ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ ሚስት እንዲያገባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ እንደ ላከውና በባረከውም ጊዜ “ከነዓናዊት ሴት አታግባ” ብሎ ትእዛዝ እንደ ሰጠው ሰማ።
7
ያዕቆብ የአባት የእናቱን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ።
8
በዚህም የከነዓናውያን ሴቶች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የቱን ያህል የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤
9
ስለዚህም ወደ እስማኤል ሄደ፣ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን፣ የነባዮትን እኅት ማዕሌትን በሚስቶቹ ላይ ተጨማሪ አድርጎ አገባ።
10
ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ።
11
ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ።
12
በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ።
13
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከጫፉ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ፣ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ፤ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።
14
ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይበዛል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ።
15
እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።”
16
ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ “በእውነት እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ።
17
እርሱም በፍርሀት፣ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህስ ሌላ ሳይሆን የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቤት መሆን አለበት፤ የሰማይ ደጅ ነው” አለ።
18
ያዕቆብም በማግስቱም ማልዶ ተነሣ፣ ተንተርሶት ያደረውን ድንጋይ አንሥቶ እንደ ሐውልት አቆመው፤ በዐናቱም ላይ የወይራ ዘይት አፈሰሰበት።
19
ያንን ቦታ ቤቴል ብሎ ሰየመው፤ ቀደም ሲል ግን የከተማዪቱ ስም ሎዛ ነበር።
20
ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበትም መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላው ምግብ፣ የምለብሰው ልብስ ቢሰጠኝ
21
ወደ አባቴ ቤትም በደኅና ቢመልሰኝ፣ እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ይሆናል፤
22
ይህ ሐውልት አድርጌ ያቆምሁት ድንጋይ፣ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝም ሀብት ሁሉ፣ ከዐሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ።”
← Chapter 27
Chapter 29 →