bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Genesis 21
Genesis 21
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረት ሣራን ዐሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት።
2
ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት።
3
አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይስሐቅ አለው።
4
አብርሃም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባዘዘው መሠረት ልጁን ይስሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው።
5
አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ።
6
ሣራም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይሥቃል” አለች።
7
ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች።
8
ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ።
9
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይስሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤
10
አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርልኝ፤ ምንም ቢሆን የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ውርስ አይካፈልም አለች።”
11
እስማኤል ልጁ ስለሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው።
12
እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ።
13
የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።”
14
በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር።
15
በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው።
16
ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር።
17
እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ።
18
ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።”
19
እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።
20
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከልጁ ጋር ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ።
21
በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብፅ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው።
22
በዚያን ጊዜ አቢሜሊክ ከሰራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአንተ ጋር ነው።
23
እንግዲህ እኔንና ልጆቼን፣ ዘሬንም በመሸንገል አንዳች ክፉ ነገር እንዳታደርስብን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ማልልኝ። እኔ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ፣ አንተም ለእኔና በእንግድነት ለተቀመጥህባት ለዚህች ምድር ቸርነት አድርግ።”
24
አብርሃምም፣ “እሺ፤ እምላለሁ” አለ።
25
ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮች ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጕድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት።
26
አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው።
27
ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ።
28
አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤
29
አቢሜሌክም፣ “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለይተህ ለብቻ ያቆምሃቸው ለምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው።
30
አብርሃምም፣ “ይህን የውሃ ጕድጓድ የቈፈርሁ እኔ ለመሆኔ ምስክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ዕንካ ተቀበለኝ” አለው።
31
ስለዚህ ቦታው፣ ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ ቤርሳቤህ ተባለ።
32
በቤርሳቤህ የስምምነት ውል ካደረጉ በኋላ፣ አቢሜሌክና የሰራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ተመለሱ።
33
አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የዘላለም አምላክን (ኤል ኦላም) ስም ጠራ።
34
አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረጅም ጊዜ በእንግድነት ኖረ።
← Chapter 20
Chapter 22 →