bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Genesis 19
Genesis 19
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ መግቢያ በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም መላእክቱን ሲያይ ሊቀበላቸው ብድግ አለ፤ በግምባሩም ወደ ምድር ተደፍቶ እጅ ነሣቸው።
2
እርሱም፣ “ጌቶቼ፤ እባካችሁ ወደ እኔ ወደ ባሪያችሁ ቤት ጎራ በሉ፤ ከዚያም እግራችሁን ታጠቡ፤ ዐድራችሁም ጧት በማለዳ ጕዟችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው። እነርሱም፣ “አይሆንም፤ እዚሁ አደባባይ ላይ እናድራለን” አሉት።
3
ሎጥ ግን አጥብቆ ስለ ለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚያም ቂጣ ጋግሮ አቀረበላቸውና በሉ።
4
ከመተኛታቸውም በፊት፣ የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከየአካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት።
5
ሎጥንም ጠርተው፣ “በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን” አሉት።
6
ሎጥም ሊያነጋግራቸው ወደ ውጭ ወጣ፤ መዝጊያውን ከበስተ ኋላው ዘግቶ፣
7
እንዲህ አለ፤ “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ።
8
እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።”
9
እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰድዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳናደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ።
10
ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ።
11
ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ።
12
ሁለቱ ሰዎችም ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች አሉህ? ዐማቾች፣ ወንዶችና ሴቶች ወይም ሌሎች ዘመዶች ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤
13
ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው። በሕዝቦቿ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበው ጩኸት ታላቅ በመሆኑ፣ እንድናጠፋት እግዚአብሔር ልኮናል።”
14
ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው።
15
ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋር አብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት።
16
ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው።
17
እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው።
18
ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤
19
እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደ ሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል።
20
እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።”
21
እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም።
22
አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ።
23
ሎጥ ዞዓር ሲደርስ ፀሓይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር።
24
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰዶምና በገሞራ ላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው።
25
እነዚያንም ከተሞችና ረባዳውን ምድር በሙሉ፣ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፣ የምድሩን ቡቃያ ሳይቀር ገለባበጠው።
26
የሎጥ ሚስት ግን ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች።
27
አብርሃም በማግስቱም፣ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ቦታ ሄደ።
28
ሰዶምንና ገሞራን፣ እንዲሁም በረባዳው ስፍራ የሚገኘውን ምድር ሁሉ ቍልቍል ተመለከተ፤ ከእቶን የሚወጣ የመሰለ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ከምድሪቱ ወደ ላይ ሲትጐለጐል አየ።
29
እንደዚህ አድርጎ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን ዐሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው።
30
ሎጥ በዞዓር መኖርን ስለ ፈራ፣ ከዚያ ተነሥቶ ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሄደ፤ መኖሪያውንም ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ አደረገ።
31
አንድ ቀን ታላቂቱ ልጅ፣ ታናሺቱን እንዲህ አለቻት፤ “አባታችን አርጅቷል፤ በምድር ሁሉ እንደሚኖሩ ሰዎች ወግ አብሮን የሚተኛ ወንድ በአካባቢያችን የለም።
32
ስለዚህ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፤ የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ዘር ከአባታችን እናትርፍ።”
33
በዚያችም ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ትልቋ ልጁ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።
34
በማግስቱም ታላቂቱ ልጅ ታናሺቱን፣ “እኔ ትናንትና ማታ ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ፤ ዛሬም እንደ ገና የወይን ጠጅ እናጠጣው፤ አንቺም ደግሞ ከእርሱ ዘንድ ገብተሽ ተኚ፤ በዚህም የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ከአባታችን ዘር ማትረፍ እንችላለን” አለቻት።
35
በዚያችም ምሽት ደግሞ አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ትንሿ ልጁም ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።
36
ስለዚህ ሁለቱም የሎጥ ሴት ልጆች ከአባታቸው አረገዙ።
37
ትልቋ ልጁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ ሞዓባውያን አባት ነው።
38
ትንሿ ልጁም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ አሞናውያን አባት ነው።
← Chapter 18
Chapter 20 →