bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Ezekiel 37
Ezekiel 37
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም በእግዚአብሔር መንፈስ አወጣኝ፤ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ ሸለቆውም በዐጥንቶች ተሞልቶ ነበር።
2
በእነርሱም መካከል ወደ ፊትና ወደ ኋላ አመላለሰኝ፤ በሸለቆውም ወለል ላይ በጣም የደረቁ እጅግ ብዙ ዐጥንቶች አየሁ።
3
እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ብቻ ታውቃለህ” አልሁ።
4
ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንት ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ!
5
ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ።
6
ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቈዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”
7
ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ።
8
እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቈዳም ሸፍኗቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም።
9
ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’ ”
10
ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11
ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ዐጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ የለንም፤ ተቈርጠናል።’
12
ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።
13
ከዚያም እናንተ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን ከፍቼ ሳወጣችሁ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14
መንፈሴን በውስጣችሁ አስቀምጣለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ፣ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፤ ይላል እግዚአብሔር ።’ ”
15
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
16
“የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ በትር ወስደህ፣ ‘የይሁዳና የተባባሪዎቹ የእስራኤላውያን’ ብለህ ጻፍበት። ከዚያም ሌላ በትር ወስደህ፣ ‘የኤፍሬም፣ የዮሴፍና የተባባሪዎቹ የእስራኤል ቤት ሁሉ’ ብለህ ጻፍበት።
17
እንደ አንድ በትር ይሆኑ ዘንድ በእጅህ ላይ አጋጥመህ ያዛቸው።
18
“የአገርህ ልጆች፣ ‘ይህስ ምን ማለትህ እንደ ሆነ አትነግረንምን?’ ብለው ሲጠይቁህ፣
19
እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትርና የተባባሪዎቹን የእስራኤላውያንን ነገድ በትር እወስዳለሁ፤ ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥሜ አንድ ወጥ በትር አደርጋቸዋለሁ፤ እነርሱም በእጄ አንድ በትር ይሆናሉ።’
20
የጻፍህባቸውን በትሮች ከፊት ለፊታቸው ያዝ፤
21
እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
22
በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ በሁሉም ላይ አንድ ንጉሥ ይነግሣል፤ ከእንግዲህም ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ መንግሥታቸውም ከሁለት አይከፈልም።
23
በጣዖቶቻቸው፣ በአጸያፊ ምስሎቻቸው ወይም በማንኛውም ኀጢአት ራሳቸውን አያረክሱም፤ ነገር ግን እኔን በመተው ከሠሩት ኀጢአት ሁሉ አድናቸዋለሁ፤ አነጻቸዋለሁም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።
24
“ ‘ባሪያዬ ዳዊት በላያቸው ይነግሣል፤ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል፤ ሕጌን ይከተላሉ፤ ሥርዐቴንም በጥንቃቄ ይጠብቃሉ።
25
አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል።
26
ከእነርሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ቃል ኪዳኑም የዘላለም ይሆናል። አጸናቸዋለሁ፤ አበዛቸዋለሁ፤ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘላለም አኖራለሁ።
27
ማደሪያዬ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
28
መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሚሆንበት ጊዜ፣ አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ቀደስሁ ያውቃሉ።’ ”
← Chapter 36
Chapter 38 →