bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Ezekiel 33
Ezekiel 33
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2
“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በምድር ላይ ሰይፍን ሳመጣ፣ የምድሪቱ ሕዝብ ከሰዎቻቸው አንዱን መርጠው ጕበኛ ቢያደርጉት፣
3
እርሱም በምድሪቱ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ቢነፋ፣
4
ከዚያም ማንም መለከቱን ሰምቶ ባይጠነቀቅ፣ ሰይፍም መጥቶ ሕይወቱን ቢያጠፋ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል።
5
የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባለመጠንቀቁ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ግን ራሱን ባዳነ ነበር።
6
ነገር ግን ጕበኛ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ሳይነፋ ቢቀርና ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት ሰይፍ ቢያጠፋ፣ ያ ሰው ስለ ኀጢአቱ ይወሰዳል፤ ጕበኛውን ግን ስለ ሰውየው ደም ተጠያቂ አደርገዋለሁ።’
7
“የሰው ልጅ ሆይ፤ አንተን ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው።
8
ክፉውን፣ ‘አንተ ክፉ ሰው፤ በርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ስለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ።
9
ነገር ግን ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው እሺ ባይል፣ እርሱ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ራስህን አድነሃል።
10
“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘እንዲህ ትላላችሁ፤ “በደላችንና ኀጢአታችን ከብዶናል፤ ከዚህም የተነሣ ልንጠፋ ነው፤ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን?” ’
11
እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’
12
“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች እንዲህ በላቸው፤ ‘ጻድቅ ሰው ትእዛዝን በተላለፈ ጊዜ የቀድሞ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛ ሰው ከኀጢአቱ ከተመለሰ፣ ከቀድሞ ክፋቱ የተነሣ አይጠፋም። ጻድቅ ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ በቀድሞ ጽድቁ ምክንያት በሕይወት እንዲኖር አይደረግም።’
13
ጻድቁን ሰው በርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለው፣ እርሱም ጽድቁን ተማምኖ ክፋት ቢሠራ፣ ከጽድቅ ሥራው አንዱም አይታሰብለትም፤ በኀጢአቱም ምክንያት ይሞታል።
14
እንዲሁም ክፉውን ሰው፣ ‘በርግጥ ትሞታለህ’ ብለው፣ እርሱም ከኀጢአቱ ተመልሶ ቀና የሆነውንና ትክክለኛውንም ነገር ቢያደርግ፣
15
ለሰጠው ብድር የተቀበለውን መያዣ ቢመልስ፣ የሰረቀውንም መልሶ ቢሰጥ፣ ሕይወት የሚሰጡትን ትእዛዞች ቢከተል፣ ክፉ ነገርንም ባያደርግ፣ በርግጥ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ አይሞትምም።
16
ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17
“ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው።
18
ጻድቅ ሰው የጽድቁን ሥራ ትቶ ክፉ ነገር ቢያደርግ፣ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል።
19
ክፉም ሰው ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል።
20
ይሁን እንጂ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”
21
በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፣ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለኝ።
22
ሰውየው ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት፣ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ላይ ነበረች፤ በማለዳም ሰውየው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ፤ ከዚያ በኋላ ዝም አላልሁም።
23
ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
24
“የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ።
25
ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈስሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ?
26
በሰይፋችሁ ትመካላችሁ፤ አስጸያፊ ነገሮችን ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት ታረክሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?’
27
“እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተረፉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በገጠር ያሉትን ቦጫጭቀው እንዲበሏቸው ለዱር አራዊት እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽግና በዋሻ ያሉትም በቸነፈር ይሞታሉ።
28
ምድሪቱን ጠፍና ባድማ አደርጋታለሁ፤ የምትመካበት ጕልበቷ እንዳልነበረ ይሆናል፤ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ።
29
ካደረጓቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሣ፤ ምድሪቱን ጠፍና ባድማ በማደርግበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’
30
“አንተን በሚመለከት፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ የአገርህ ሰዎች በየቤቱ በርና ግድግዳ ሥር ሆነው ስለ አንተ ይነጋገራሉ፤ እርስ በራሳቸውም እንዲህ ይባባላሉ፤ ‘ኑና ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት እንስማ።’
31
ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ሕዝቤ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህንም ለመስማት ከፊትህ ይቀመጣሉ፤ ነገር ግን አይፈጽሙትም። በከንፈራቸው ብዙ ፍቅርን ይገልጣሉ፤ ልባቸው ያረፈው ግን ተገቢ ባልሆነ ጥቅም ላይ ነው።
32
ቃልህን ሰምተው ሥራ ላይ የማያውሉት በመሆናቸው፣ አንተ ለእነርሱ በአማረ ድምፅ የፍቅር ዘፈን የሚዘፍን፣ በዜማ መሣሪያም አሳምሮ የሚጫወት ሙዚቀኛ ሆነህላቸዋል።
33
“ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ደግሞም በርግጥ ይሆናል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ፣ ያውቃሉ።”
← Chapter 32
Chapter 34 →