bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 4
Exodus 4
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘ እግዚአብሔር (ያህዌ) አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ።
2
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው፤ እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው።
3
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው። ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ።
4
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች።
5
እግዚአብሔርም (ያህዌ) “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው።
6
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች።
7
“አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች።
8
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ።
9
እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።”
10
ሙሴም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ፣ “ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው።
11
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አይደለሁምን?
12
በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው።
13
ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ (አዶናይ) ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።
14
በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል።
15
ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ እረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ።
16
አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል።
17
ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።”
18
ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብፅ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው።
19
ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው።
20
ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብፅ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርንም (ኤሎሂም) በትር በእጁ ይዞ ነበር።
21
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብፅ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ።
22
ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤
23
ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ”
24
ሙሴ በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር።
25
ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው።
26
ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው።
27
እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አገኘው፤ ሳመውም።
28
ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው።
29
ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤
30
አሮንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ።
31
ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ የሚገድደው መሆኑንና መከራቸውን ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።
← Chapter 3
Chapter 5 →