bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 34
Exodus 34
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርካቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ።
2
በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤
3
ከአንተ ጋር ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።”
4
ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርቦ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶችም በእጆቹ ያዘ።
5
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ።
6
እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “ እግዚአብሔር (ያህዌ) ርኅሩኅ ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣
7
ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”
8
ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤
9
“አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ (አዶናይ) ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።”
10
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው አብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደ ሆነ ያያሉ።
11
ዛሬ የማዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ።
12
ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል።
13
መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ ፤ የአሼራ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ።
14
ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።
15
“በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ።
16
ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሷቸዋል።
17
“ቀልጠው የሚሠሩ አማልክትን አታብጅ።
18
“የቂጣን በዓል አክብር። እንዳዘዝሁህም ለሰባት ቀን እርሾ ያልገባበት ቂጣ ብላ፤ ይህንም በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና።
19
“የመንጋህ ወይም የበግና የፍየልህ፣ የቀንድ ከብትህ ተባዕት በኵር ሁሉ ሳይቀር፣ ከማሕፀን በኵር ሆኖ የሚወጣ ሁሉ የእኔ ነው።
20
የአህያን በኵር በበግ ጠቦት ዋጀው፤ ካልዋጀኸው ግን ዐንገቱን ስበረው። በኵር ወንድ ልጆችህን ሁሉ ዋጅ። “ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።
21
“ስድስት ቀን ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍ፤ በዕርሻና በመከር ወቅት እንኳ ቢሆን ማረፍ አለብህ።
22
“የሰባቱን ሱባዔ በዓል ከስንዴው መከር በኵራቶች ጋር፣ እንዲሁም የመክተቻ በዓልን በዓመቱ መጨረሻ ላይ አክብር።
23
በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) በጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ፊት ይቅረብ።
24
አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም።
25
“እርሾ ካለው ከማንኛውም ነገር ጋር የደም መሥዋዕት ለእኔ አታቅርብ፤ ከፋሲካ በዓል የተረፈው መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይቈይ።
26
“የዐፈርህን ምርጥ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቤት አምጣ። “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።”
27
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና” አለው።
28
ሙሴ እህል ሳይበላ፣ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ።
29
ሙሴ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር።
30
አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ባዩት ጊዜ ፊቱ ያበራ ነበር፤ ወደ እርሱ ለመቅረብም ፈርተው ነበር።
31
ሙሴ ግን ጠራቸው፤ ስለዚህ አሮንና የማኅበሩ መሪዎች ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም አናገራቸው።
32
ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ የሰጠውን ትእዛዞች ሁሉ ሰጣቸው።
33
ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ።
34
ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሀልዎት በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ግን፣ እስከሚወጣ ድረስ መሸፈኛውን ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ የታዘዘውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው።
35
ፊቱ የሚያበራ መሆኑን አዩ፤ ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ለመነጋገር ተመልሶ እስኪሄድ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ በፊቱ ላይ ያደርግ ነበር።
← Chapter 33
Chapter 35 →