bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 23
Exodus 23
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
“የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ።
2
“ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋር ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም።
3
በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ።
4
“የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እርሱ መልሰው።
5
የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ።
6
“በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት።
7
ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ትክክለኛውን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና።
8
“ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።
9
“መጻተኛውን አትጨቍን፤ በግብፅ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።
10
“ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤
11
ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከእርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ።
12
“ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።
13
“ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።
14
“በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ።
15
“ያልቦካ የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና። “ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።
16
“በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር። “በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር።
17
“በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ፊት ይቅረብ።
18
“የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋር አድርገህ ለእኔ አታቅርብ። “የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቈይ።
19
“የምድርን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምጣ። “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።
20
“እነሆ፤ በጕዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ።
21
በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ አድምጠው፤ አታምፅበት። ስሜ በእርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም።
22
የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ።
23
መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ።
24
ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር።
25
አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ።
26
በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረዥም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።
27
“በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ።
28
ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰድዳለሁ።
29
ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ ባድማ ሆና የዱር አራዊት ይበዙባችኋል።
30
ቍጥርህ ጨምሮ ምድሪቱን ለመውረስ እስክትበቃ ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊታችሁ አባርራቸዋለሁ።
31
“ድንበርህን ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፣ ከምድረ በዳው እስከ ወንዙ ድረስ አደርገዋለሁ፤ በምድሪቱም ላይ የሚኖሩትን ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም አሳድደህ ከፊትህ ታስወጣቸዋለህ።
32
ከእነርሱም ሆነ ከአማልክቶቻቸው ጋር ኪዳን አታድርግ።
33
በምድርህ ላይ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ አለዚያ እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ አማልክታቸውን ማምለክ በርግጥ ወጥመድ ይሆንብሃልና።”
← Chapter 22
Chapter 24 →