bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 20
Exodus 20
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤
2
“ከግብፅ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) እኔ ነኝ።
3
“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።
4
በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ።
5
አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) የሚጠሉኝን ልጆች ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤
6
ነገር ግን ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ፍቅርን የማሳይ ነኝ።
7
የእግዚአብሔር (ያህዌ) የአምላክህን ስም ያለ አግባብ አታንሣ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን ያለ አግባብ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና።
8
የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብር።
9
ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን።
10
ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕለቱ አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ወይም ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በግቢህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም።
11
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፣ በሰባተኛው ቀን ዐርፏልና። ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም።
12
አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።
13
አትግደል።
14
አታመንዝር።
15
አትስረቅ።
16
በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
17
የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።”
18
ሕዝቡም መብረቁንና ነጐድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሀት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤
19
ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንዲናገረን አታድርግ፤ አለዚያ መሞታችን ነው” አሉት።
20
ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍርሀት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው።
21
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።
22
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤
23
ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ።
24
“ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በእርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ።
25
ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና።
26
ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል።’
← Chapter 19
Chapter 21 →