bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 12
Exodus 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን በግብፅ እንዲህ አላቸው፤
2
“ይህ ወር ለእናንተ የወር መጀመሪያ፣ የዓመቱም መጀመሪያ ይሁንላችሁ።
3
ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህን ንገሩ፤ ይህ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ጠቦት ለቤተ ሰቡ፣ አንዳንድ ጠቦት ለአባቱ ቤት ያዘጋጅ።
4
ማንኛውም ቤተ ሰብ ለአንድ ሙሉ ጠቦት ቍጥሩ አነስተኛ ከሆነ፣ በጎረቤት ያሉትን ሰዎች ቍጥር እስከ ቅርብ ከሆነው ጋር መካፈል ይኖርበታል፤ እያንዳንዱ ሰው በሚበላው መጠንም ምን ያህል ጠቦት እንደሚያስፈልግ መወሰን ይኖርባችኋል።
5
የምትመርጡት ጠቦት በግ ወይም ፍየል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት መሆን አለበት።
6
ወሩ በገባ እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው።
7
ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጕበን ይቀቡ።
8
ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት።
9
ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት።
10
ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል።
11
ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ በዐጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ ነው።
12
“እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ምድር ላይ ዐልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብፅን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
13
ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን ዐልፋለሁ፤ ግብፅን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።
14
“ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።
15
ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበትን ቂጣ ብሉ፤ በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በእነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ።
16
በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል።
17
“የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብፅ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት።
18
ከመጀመሪያው ወር ከዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ እርሾ የሌለበት ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ።
19
ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ።
20
እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ነው መብላት ያለባችሁ።”
21
ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቶሎ ሄዳችሁ ለየቤተ ሰቦቻችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን በግ ዕረዱ።
22
ከዚያም ጭብጥ የሂሶጵ ቅጠል በመውሰድ፣ በሳሕን ውስጥ ካለው ደም ነክራችሁ የየቤቶቻችሁን ጕበንና ግራ ቀኝ መቃኑን ቀቡ። ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ።
23
እግዚአብሔር (ያህዌ) ግብፃውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጕበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያንን ደጃፍ ዐልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታችሁ ገብቶ እንዳይገድላችሁ ይከለክለዋል።
24
“እናንተም ሆነ ልጆቻችሁ ይህን መመሪያ ቋሚ ሥርዐት አድርጋችሁ ትታዘዛላችሁ።
25
እግዚአብሔር (ያህዌ) እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ይህን ሥርዐት ጠብቁ።
26
ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣
27
‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት ዐልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም።
28
እስራኤላውያንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።
29
እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ ምድር በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ፣ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ እስካለው እስረኛ የበኵር ልጅ ድረስ ያለውንና የእንስሳቱን በኵሮች ሁሉ ቀሠፋቸው።
30
ፈርዖን፣ ሹማምቱና የግብፅ ሕዝብ በሙሉ ሌሊቱን ከመኝታቸው ተነሡ፤ እነሆ በመላዪቱ ግብፅ ልቅሶና ዋይታ ነበር፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረምና።
31
ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ሌሊቱን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ተነሡ፤ እናንተና እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤
32
እንዳላችሁት የበግና የፍየል መንጋችሁን፣ የቀንድና የጋማ ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።”
33
ግብፃውያን አገራቸውን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡላቸው እስራኤላውያንን አጣደፏቸው። “አለዚያማ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉ።
34
ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሖ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ።
35
እስራኤላውያን ሙሴ እንዳዘዛቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎች፣ እንደዚሁም ልብስ እንዲሰጧቸው ግብፃውያኑን ጠየቋቸው።
36
እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያን ፊት ለእስራኤላውያን ሞገስ ስለሰጣቸው፣ የጠየቋቸውን ሁሉ ሰጧቸው፤ ስለዚህ የግብፃውያንን ንብረት በዝብዘው ወሰዱ።
37
እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ። ከሴቶቹና ከልጆቹ ሌላ፣ ስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ ወንዶች ነበሩ።
38
ከእነርሱም ጋር ቍጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ አብሯቸው ወጣ፤ እንዲሁም አያሌ የበግ፣ የፍየል፣ የጋማና የቀንድ ከብት መንጋ ይዘው ወጡ።
39
ከግብፅ ይዘው ከወጡት ሊጥ ያልቦካ ቂጣ ጋገሩ፤ ሊጡ አልቦካም ነበር፤ ምክንያቱም ከግብፅ በጥድፊያ እንዲወጡ ስለተደረጉ፣ ለራሳቸው ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ አልነበራቸውም።
40
እንግዲህ እስራኤላውያን በግብፅ የኖሩበት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር።
41
ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰራዊት ሁሉ ግብፅን ለቅቆ ወጣ።
42
እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚያች ሌሊት እነርሱን ከግብፅ ለማውጣት ዘብ የቆመበት በመሆኑ፣ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ያከብሩ ዘንድ፣ በዚያች ሌሊት እስራኤላውያን ሁሉ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።
43
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዐት እንዲህ ነው፤ ባዕድ የሆነ ሰው ከፋሲካው ምግብ አይብላ፤
44
በገንዘብ የገዛኸው ማንኛውም ባሪያ ከገረዝኸው በኋላ መብላት ይችላል፣
45
ነገር ግን ለጊዜው የተቀመጠ እንግዳና ቅጥር ሠራተኛ መብላት የለበትም።
46
“ምግቡ በአንድ ቤት ውስጥ መበላት አለበት፤ ምንም ሥጋ ከቤት እንዳይወጣ፤ ምንም ዐጥንት እንዳትሰብሩ።
47
የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በዓሉን ማክበር ይኖርበታል።
48
“በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የፋሲካ በዓል ማክበር ቢፈልግ፣ በቤተ ሰቡ ያሉት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው፤ ከዚያም እንደ ተወላጅ ተቈጥሮ የሥርዐቱ ተካፋይ ይሁን። ያልተገረዘ ወንድ ግን የፋሲካን ምግብ አይብላ።
49
ይህም ሕግ በዜጋውም ሆነ በመካከላችሁ በሚኖሩት መጻተኞች ላይ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።”
50
እስራኤላውያን በሙሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ።
51
በዚያችው ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው አድርጎ ከግብፅ ምድር አወጣቸው።
← Chapter 11
Chapter 13 →