bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 10
Exodus 10
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤
2
ይኸውም ግብፃውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔንም እንድታውቁ ነው።”
3
ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው።
4
እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ።
5
አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል።
6
የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብፃውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።
7
የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብፅ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን?” አሉት።
8
ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ።
9
ሙሴም፣ “ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ልናከብር ስለሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።
10
ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር እንድትሄዱ እለቅቃችኋለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ነገር ግን ተንኰል አስባችኋል።
11
አይሆንም፤ ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።
12
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወርር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብፅ አገር ላይ ዘርጋ” አለው።
13
ስለዚህ ሙሴ በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) በዚያን ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግሥቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ።
14
እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም።
15
ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን፣ በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠርገው በሉ። በግብፅ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።
16
ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ያህዌ) በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤
17
እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለምኑልኝ።”
18
ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ።
19
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው፤ ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር ከተታቸው፤ በግብፅ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም።
20
እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።
21
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በግብፅ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው።
22
ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብፅ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ።
23
በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር።
24
ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ አብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው።
25
ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤
26
እንስሶቻችን ሁሉ አብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳ አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደ ሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።”
27
ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም።
28
ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው።
29
ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን፤ እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው።
← Chapter 9
Chapter 11 →