bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Deuteronomy 32
Deuteronomy 32
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሰማያት ሆይ፤ አድምጡ፤ እኔም እናገራለሁ፤ ምድር ሆይ፤ አንቺም የአፌን ቃል ስሚ።
2
ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትውረድ፤ ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤ በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ፣ ለጋ ተክልም ላይ እንደ ከባድ ዝናብ ይውረድ።
3
እኔ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ዐውጃለሁ፤ የአምላካችንን (ኤሎሂም) ታላቅነት አወድሱ!
4
እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።
5
በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤ ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው ።
6
አንተ ተላላና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣ ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን? አባትህ ፈጣሪህ ፣ የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን?
7
የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል።
8
ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣ የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣ በእስራኤል ልጆች ቍጥር ልክ፣ የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ፤
9
የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የገዛ ሕዝቡ፣ ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና።
10
እርሱን በምድረ በዳ፣ ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤ ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው።
11
ንስር ጐጆዋን በትና፣ በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፣ እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ፣ በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፣
12
እግዚአብሔር (ያህዌ) ብቻ መራው፤ ምንም ባዕድ አምላክ አብሮት አልነበረም።
13
በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ የዕርሻንም ፍሬ መገበው፤ ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤ ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው።
14
የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወተት፣ የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፣ የባሳንን ምርጥ አውራ በግ፣ መልካም የሆነውንም ስንዴ፣ ማለፊያውንም የወይን ጠጅ።
15
ይሹሩን ወፈረ፤ ረገጠ፤ ጠገበ፤ ሰውነቱ ደነደነ፤ ለሰለሰ፤ የፈጠረውንም አምላክ (ኤሎሂም) ተወ፤ መጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀ።
16
በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤ በአጸያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቈጡት።
17
አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፦ ላላወቋቸው አማልክት፣ ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፣ አባቶቻችሁ ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ።
18
አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤ የወለደህን አምላክ ረሳኸው።
19
እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን አይቶ ናቃቸው፤ በወንድና በሴት ልጆቹ ተቈጥቷልና።
20
እርሱም፣ “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ” አለ፤ ጠማማ ትውልድ፣ የማይታመኑም ልጆች ናቸውና።
21
አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ በከንቱ ጣዖቶቻቸው አስቈጡኝ። እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ። በማያስተውልም ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።
22
በቍጣዬ እሳት ተቀጣጥሏልና፤ እርሱ እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነድዳል። ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤ የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል።
23
“በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ። ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ።
24
የሚያጠፋ ራብ፣ በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድ መቅሠፍት እሰድድባቸዋለሁ፤ የአራዊትን ሹል ጥርስ፣ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝም እሰድድባቸዋለሁ።
25
ሰይፍ መንገድ ላይ ያስቀራቸዋል፤ ቤታቸውም ውስጥ ድንጋጤ ይነግሣል፤ ጕልማሳውና ልጃገረዷ፣ ሕፃኑና ሽማግሌው ይጠፋሉ።
26
እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ አልሁ፤
27
ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፣ ‘ድል ያደረገችው እጃችን እንጂ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፣ የጠላትን መነሣሣት ሠጋሁ።”
28
አእምሮ የጐደላቸው፣ ማስተዋልም የሌላቸው ናቸው።
29
አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡ፣ መጨረሻቸውም ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነበር።
30
መጠጊያ ዐለታቸው ካልሸጣቸው፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ካልተዋቸው በቀር፣ አንድ ሰው እንዴት ሺሑን ያሳድዳል? ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺሑን እንዲሸሹ ያደርጋሉ?
31
የእነርሱ መጠጊያ ዐለት እንደ እኛ መጠጊያ ዐለት አይደለምና፤ ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን አይክዱም።
32
ወይናቸው ከሰዶም ወይን፣ ከገሞራም ዕርሻ ይመጣል፤ የወይናቸው ፍሬ በመርዝ፣ ዘለላቸውም በምሬት የተሞላ ነው።
33
ወይናቸው የእባብ መርዝ፣ የመራዥ እባብም መርዝ ነው።
34
“ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ ያለ፣ በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?
35
በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤ ጊዜው ሲደርስ እግራቸው ይሰናከላል፤ የመጥፊያቸው ቀን ቀርቧል፤ የሚመጣባቸውም ፍርድ ፈጥኖባቸዋል።”
36
ኀይላቸው መድከሙን፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይራራል።
37
እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣ እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ?
38
የመሥዋዕታቸውን ሥብ የበሉ፣ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው? እስቲ ይነሡና ይርዷችሁ! እስቲ መጠለያ ይስጧችሁ!
39
“እኔ ራሴ እርሱ እንደ ሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤ አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።
40
እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤ ለዘላለምም ሕያው እንደ ሆንሁ እናገራለሁ፤
41
የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ስዬ፣ እጄ ለፍርድ ስትይዘው፣ ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤ የሚጠሉኝንም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ።
42
ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፣ ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤ ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች፣ የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።”
43
አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ ፤ እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤ ጠላቶቹንም ይበቀላል። ምድሪቱንና ሕዝቡን ይቤዣቸዋልና።
44
ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋር መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃሎች በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ።
45
ሙሴም እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣
46
እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ።
47
ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ በምትወርሷትም ምድር ረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።
48
በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
49
“ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር፣ ከዓባሪም ተራሮች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ናባው ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓንን ምድር አሻግረህ ተመልከት።
50
ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተሰበሰበ ሁሉ፣ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፤ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ።
51
ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ፣ በቃዴስ በመሪባ ውሃ አጠገብ በእኔ ላይ መታመናችሁን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደላችሁና ቅድስናዬንም በእስራኤላውያን መካከል ስላላከበራችሁ ነው።
52
ስለዚህ ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።”
← Chapter 31
Chapter 33 →