bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Deuteronomy 26
Deuteronomy 26
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፣ ስትወርሳትና ስትኖርባት፣
2
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ሰብል ሁሉ፣ በኵራት ወስደህ በቅርጫት ውስጥ አድርገው፤ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ፤
3
በዚያም ወቅት ለሚያገለግለው ካህን፣ “ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእኛ ሊሰጠን ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት እናገራለሁ” በለው።
4
ካህኑም ቅርጫቱን ከእጅህ ተቀብሎ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ፊት ለፊት ያስቀምጠዋል።
5
አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) ፊት እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፤ “አባቴ ዘላን ሶርያዊ ነበር፤ ከጥቂት ሰዎችም ጋር ወደ ግብፅ ወረደ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ፣ ኀያልና ቍጥሩ የበዛ ሕዝብ ሆነ።
6
ግብፃውያን ግን ከባድ ሥራ በማሠራት አንገላቱን፤ አሠቃዩንም።
7
ከዚያ በኋላ የአባቶቻችን አምላክ (ያህዌ) ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ጩኸታችንን ሰማ፤ ጕስቍልናችንን፣ ድካማችንንና የተፈጸመብንን ግፍ ተመለከተ።
8
ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ በታላቅ ድንጋጤ፣ በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ከግብፅ አወጣን።
9
ወደዚህ ስፍራ አመጣን፤ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ይህችን ምድር ሰጠን፤
10
አሁንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ እነሆ፤ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን በኵራት አምጥቻለሁ።” ቅርጫቱንም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት አስቀምጠው፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ስገድ።
11
ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው መጻተኛ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአንተና ለቤትህ በሰጠው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ይበላችሁ።
12
የዐሥራት ዓመት የሆነውን የሦስተኛውን ዓመት ምርት አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ፣ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው፤
13
ከዚያ በኋላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲህ በል፤ “በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት የተቀደሰውን ክፍል ከቤቴ አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም።
14
በሐዘን ላይ ሳለሁ፣ ከተቀደሰው ክፍል ላይ ምንም አልበላሁም፤ ባልነጻሁበትም ጊዜ ከዚሁ ላይ ያነሣሁትም ሆነ ለሙታን ያቀረብሁት ምንም ነገር የለም፤ አምላኬን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ታዝዣለሁ፤ ያዘዝኸኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ።
15
ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል በገባኸው መሠረት፣ ለእኛ የሰጠኸንን ይህችን ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ባርክ።”
16
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህን ሥርዐትና ሕግ ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ ያዝዝሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህ፣ በፍጹምም ነፍስህ ትፈጽመው ዘንድ ተጠንቀቅ።
17
እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) እንደ ሆነ በመንገዱም እንደምትሄድ፣ ሥርዐቱን፣ ትእዛዙንና ሕጉን እንደምትጠብቅና እንደምትታዘዝለት በዛሬዪቱ ዕለት ተናግረሃል።
18
እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ፣ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፣ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት ተናግሯል።
19
ከፈጠራቸው ሕዝቦች ሁሉ በላይ በምስጋና፣ በስም፣ በክብርም ከፍ እንደሚያደርግህና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ እንደምትሆን ተናግሯል።
← Chapter 25
Chapter 27 →