bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Deuteronomy 21
Deuteronomy 21
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር አንድ ሰው ተገድሎ ሜዳ ላይ ቢገኝና ገዳዩም ማን እንደ ሆነ ባይታወቅ፣
2
ሽማግሌዎችህና ዳኞችህ ወጥተው ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ አንሥቶ በአቅራቢያው እስካሉት ከተሞች ድረስ ያለውን ርቀት ይለኩ።
3
ከዚያም ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ በጣም ቅርብ የሆነችው ከተማ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችና ቀንበር ያልተጫነባትን ጊደር ይዘው፣
4
ከዚያ በፊት ታርሶ ወይም ተዘርቶበት ወደማይታወቅ ወራጅ ውሃ ወዳለበት ሸለቆ ያምጡት። በዚያ ሸለቆም የጊደሪቱን ዐንገት ይስበሩ፤
5
እንዲያገለግሉና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም እንዲባርኩ፣ በማንኛውም የክርክርና የጥቃት ጕዳዮች ሁሉ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መርጧቸዋልና የሌዊ ልጆች ካህናቱ ወደ ፊት ይቅረቡ።
6
ከዚያም ሬሳው በተገኘበት አቅራቢያ ባለችው ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሁሉ፣ በሸለቆው ውስጥ፣ ዐንገቷ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ይታጠቡ።
7
እንዲህም ብለው ይናገሩ፤ “እጆቻችን ደም አላፈሰሱም፤ ድርጊቱ ሲፈጸምም ዐይኖቻችን አላዩም።
8
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ስለ ተቤዠኸው ሕዝብህ ስለ እስራኤል ብለህ ይህን ስርየት ተቀበል፤ ሕዝብህንም በፈሰሰው ንጹሕ ደም በደለኛ አታድርግ።” ስለ ፈሰሰውም ደም ስርየት ይደረግላቸዋል።
9
አንተም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቀና የሆነውን ስታደርግ፣ የንጹሑን ደም የማፍሰስ በደልን ከመካከልህ ታስወግዳለህ።
10
ከጠላቶችህ ጋር ጦርነት ልትገጥም ወጥተህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶህ በማረክህ ጊዜ፣
11
ከምርኮኞቹ መካከል መልከ መልካም ሴት አይተህ ብትማርክህ፣ ሚስትህ ልታደርጋት ትችላለህ።
12
ወደ ቤትህ ውሰዳት፤ ጠጕሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቍረጥ።
13
ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፣ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፣ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች።
14
በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፣ ወደምትፈልገው እንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና ልትሸጣት ወይም እንደ ባሪያ ልትቈጥራት አይገባህም።
15
አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፣ አንደኛዋን የሚወድዳት፣ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፣ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኵር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወድዳት ሚስቱ ቢሆን፣
16
ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፣ የብኵርናን መብት ከማይወድዳት ሚስቱ ከወለደው በኵር ልጅ ገፎ፣ ከሚወድዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤
17
ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኵርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኀይል መጀመሪያ ነውና፣ የብኵርና መብት የራሱ ነው።
18
አንድ ሰው፣ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፣ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣
19
አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፤
20
“ይህ ልጃችን እልከኛና ዐመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው” ብለው ለአለቆች ይንገሯቸው።
21
ከዚያም በኋላ የከተማዪቱ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ ክፉውንም ከመካከልህ አስወግድ፤ እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል።
22
አንድ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ፈጽሞ ቢገደልና በድኑ በዕንጨት ላይ ቢሰቀል፣
23
በድኑን በዕንጨት ላይ እንደ ተሰቀለ አታሳድረው፤ ምክንያቱም በዕንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ የተረገመ ነውና፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር እንዳታረክስ፣ በዚያኑ ዕለት ቅበረው።
← Chapter 20
Chapter 22 →