bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Deuteronomy 15
Deuteronomy 15
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት አድርግ።
2
አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ እያንዳንዱ አበዳሪ ለእስራኤላዊ ባልንጀራው ያበደረውን ይተውለት፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የዕዳ ምሕረት ዐውጇልና፣ አበዳሪው፣ እስራኤላዊ ባልንጀራውን ወይም ወንድሙን ዕዳውን እንዲከፍለው አይጠይቀው።
3
ለባዕድ ያበደርኸውን መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ከአንተ የተበደረውን ማናቸውንም ዕዳ ግን ተወው።
4
ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤
5
ይህ የሚሆነውም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ስትከተል ብቻ ነው።
6
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም።
7
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖር፣ በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አታጨክንበት፤ ወይም እጅህን ወደ ኋላ አትሰብስብበት።
8
ይልቁንስ እጅህን ፍታለት፤ የሚያስፈልገውንም ሁሉ ቅር ሳይልህ አበድረው።
9
“ዕዳ የሚሠረዝበት ሰባተኛው ዓመት ተቃርቧል” የሚል ክፉ ሐሳብ ዐድሮብህ፣ በችግረኛ ወንድምህ ላይ እንዳትጨክንና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር፣ እርሱም በአንተ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኾ በደለኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!
10
በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠውም ልብህ አይጸጸት፤ ከዚህም የተነሣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሥራህ ሁሉና እጅህ ባረፈበት በማናቸውም ነገር ይባርክሃል።
11
በምድሪቱ ላይ ድኾች ምንጊዜም አይጠፉም፤ ስለዚህ በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞችህ፣ ለድኾችና ለችግረኞች እጅህን እንድትዘረጋ አዝዝሃለሁ።
12
ወገንህ የሆነ ዕብራዊ ወንድን ወይም ሴትን ገዝተህ ስድስት ዓመት ካገለገለህ፣ በሰባተኛው ዓመት ዐርነት አውጣው።
13
በምታሰናብተውም ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው።
14
ከመንጋህ፣ ከዐውድማህና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን ስጠው።
15
አንተም ራስህ በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን ትእዛዝ ዛሬ የምሰጥህም በዚሁ ምክንያት ነው።
16
ነገር ግን አገልጋይህ፣ አንተንና ቤተ ሰብህን ከመውደዱና ከአንተም ጋር ደስተኛ ሆኖ ከመኖሩ የተነሣ፣ “ከአንተ መለየት አልፈልግም” ቢልህ፣
17
ጆሮውን ከቤትህ መዝጊያ ላይ በማስደገፍ በወስፌ ትበሳዋለህ፤ ከዚያም ዕድሜ ልኩን አገልጋይህ ይሆናል። በሴት አገልጋይህም ላይ እንደዚሁ አድርግ።
18
አገልጋይህን ዐርነት ማውጣቱ ከባድ መስሎ አይታይህ፤ የስድስት ዓመት አገልግሎቱ፣ አንድ የቅጥር ሠራተኛ የሚሰጠው አገልግሎት ዕጥፍ ነውና። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምታደርገው ነገር ሁሉ ይባርክሃል።
19
የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎችህን ተባዕት በኵር ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቀድስ። የበሬህን በኵር አትሥራበት፤ የበግህንም በኵር አትሸልት፤
20
እርሱ በሚመርጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበሉታላችሁ።
21
አንድ እንስሳ እንከን ካለበት፣ ዐንካሳ ወይም ዕውር ወይም ደግሞ ማናቸውም ዐይነት ከባድ ጕድለት ያለበት ከሆነ፣ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አትሠዋው፤
22
በየከተሞችህም ትበላዋለህ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነውም ሆነ ያልሆነው ሰው፣ እንደ ድኵላ ወይም እንደ ዋላ ይበላዋል።
23
ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።
← Chapter 14
Chapter 16 →