bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Deuteronomy 10
Deuteronomy 10
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀርጸህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ላይ ውጣ፤ ታቦትም ከዕንጨት ሥራ።
2
እኔም አንተ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት በእነዚህኞቹ ጽላቶች ላይ እጽፋቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።”
3
ስለዚህ ከግራር ዕንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀረጽሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጆቼ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።
4
እግዚአብሔር (ያህዌ) በስብሰባው ቀን፣ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የተናገራቸውንና ቀድሞ ጽፏቸው የነበሩትን ዐሥሩን ትእዛዞች በእነዚህ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ።
5
ከዚያም ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት በሠራሁት ታቦትም ውስጥ፣ ጽላቶቹን አስቀመጥኋቸው፤ አሁንም እዚያ ናቸው።
6
እስራኤላውያን ከብኤሮት ብኔያዕቃን፣ የያዕቃን ልጆች ከቈፈሯቸው የውሃ ጕድጓዶች ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤ ልጁ አልዓዛር በእርሱ ምትክ ካህን ሆነ።
7
ከዚያም ተነሥተው ጕድጎዳ ወደ ተባለ ስፍራ፣ ቀጥሎም የውሃ ፈሳሾች ወዳሉባት ዮጥባታ ወደምትባል ምድር ተጓዙ።
8
በዚያን ጊዜ፣ ዛሬም እንደሚያደርገው ያገለግል ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት እንዲቆምና በስሙ እንዲባርክ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሌዊን ነገድ ለየ።
9
ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።
10
እኔም በመጀመሪያው ጊዜ እንዳደረግሁት፣ በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ በዚህ ጊዜም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ገና ሰማኝ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተን ሊያጠፋ አልፈቀደም።
11
ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ፣ “ሂድ፤ ለአባቶቻቸው ለመስጠት ወደ ማልሁላቸው ምድር ገብተው እንዲወርሱ ሕዝቡን ምራ” አለኝ።
12
አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣
13
መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?
14
ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በእርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነው።
15
ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) አባቶችህን ስላፈቀረ፣ ወደዳቸው፤ ዛሬም እንደ ሆነው የእነርሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከአሕዛብ ሁሉ ለይቶ መረጣችሁ።
16
ስለዚህ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙት፤ ከእንግዲህም ወዲያ ዐንገተ ደንዳና አትሁኑ።
17
አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአማልክት አምላክ (ኤሎሂም) ፣ የጌቶች ጌታ (አዶናይ) ታላቅ አምላክ (ኤሎሂም) ፣ ኀያልና የሚያስፈራ፣ አድልዎ የማያደርግ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና።
18
እርሱ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች ይፈርዳል፤ መጻተኛውንም ምግብና ልብስ በመስጠት ይወድዳል።
19
ስለዚህ እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛን ውደዱ።
20
አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፍራ፤ አምልከውም፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቅ፤ በስሙም ማል።
21
እርሱ ውዳሴህ ነው፤ በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን፣ እነዚያን ታላላቅና አስፈሪ ነገሮች ያደረገልህ አምላክህ (ኤሎሂም) ነው።
22
አባቶችህ ወደ ግብፅ ሲወርዱ ሰባ ነበሩ፤ አሁን ግን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንደ ሰማይ ከዋክብት አብዝቶሃል።
← Chapter 9
Chapter 11 →