bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Acts 23
Acts 23
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ጳውሎስም ወደ ሸንጎው ትኵር ብሎ በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ሕሊና ተመላልሻለሁ” አለ።
2
በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ።
3
ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው።
4
ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።
5
ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባለማወቄ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ተብሎ ተጽፏልና” አላቸው።
6
ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ።
7
ይህንም በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሣ፤ ሸንጎውም ለሁለት ተከፈለ።
8
ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም መናፍስትም የሉም የሚሉ ሲሆኑ፣ ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚያምኑ ነበሩ።
9
ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የኦሪት ሕግ መምህራንም ተነሥተው፣ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮትስ እንደ ሆነ ምን ይታወቃል?” በማለት አጥብቀው ተከራከሩ።
10
ጠቡ ከማየሉ የተነሣም አዛዡ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈራ፤ ስለዚህ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው ወደ ጦሩ ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ።
11
በሚቀጥለውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው።
12
በነጋም ጊዜ፣ አይሁድ ተሰብስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። በዚህ ሤራ
13
የተማማሉትም ከአርባ በላይ ነበሩ።
14
እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ አድርገናል።
15
እንግዲህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ፣ ስለ ጕዳዩ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ከእርሱ እንደምትፈልጉ አስመስላችሁ ጳውሎስን ወደ እናንተ እንዲሰድደው የጦር አዛዡን ለምኑት፤ እኛም ገና ወደዚህ ሳይደርስ ልንገድለው ዝግጁ ነን።”
16
ነገር ግን የጳውሎስ የእኅት ልጅ ስለ ሤራው በመስማቱ፣ ወደ ጦሩ ሰፈር ገብቶ ሁኔታውን ለጳውሎስ ነገረው።
17
ጳውሎስም ከመቶ አለቆቹ አንዱን ጠርቶ፣ “ይህ ልጅ ለጦር አዛዡ የሚነግረው ነገር ስላለ ወደ እርሱ ውሰደው” አለው።
18
እርሱም ወደ ጦር አዛዡ ወሰደው። የመቶ አለቃውም፣ “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ፣ ይህ ጕልማሳ የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ” አለው።
19
አዛዡም የጕልማሳውን እጅ ይዞ ለብቻው ገለል በማድረግ፣ “ልትነግረኝ የምትፈልገው ምንድን ነው?” አለው።
20
ልጁም እንዲህ አለው፤ “አይሁድ ስለ እርሱ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የፈለጉ በመምሰል፣ ጳውሎስን ነገ ሸንጎው ፊት እንድታቀርብላቸው ሊለምኑህ ተስማምተዋል።
21
ስለዚህ እሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑት ሊገድሉት አድፍጠው እየጠበቁት ነው፤ ደግሞም እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን መልስ እየተጠባበቁ ነው።”
22
የጦር አዛዡም፣ “ይህን ለእኔ የገለጥህልኝን ነገር ለማንም እንዳትናገር” ብሎ ጕልማሳውን አስጠንቅቆ አሰናበተው።
23
ከዚያም ከመቶ አለቆቹ ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት፣ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮች፣ ሰባ ፈረሰኞችና ሁለት መቶ ባለ ጦር ጭፍራ አዘጋጁ፤
24
ደግሞም ጳውሎስ ተቀምጦበት ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ በደኅና የሚደርስበት ከብት ይዘጋጅ።”
25
ደብዳቤም ጻፈ፤ እንዲህ የሚል፦
26
ከቀላውዴዎስ ሉስዩስ፤ ለክቡር አገረ ገዥ ለፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን።
27
አይሁድ ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ነገር ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ፣ ከወታደሮቼ ጋር ደርሼ አተረፍሁት።
28
ለምን ሊከስሱት እንደ ፈለጉ ለማወቅም ወደ ሸንጓቸው አቀረብሁት።
29
የተከሰሰውም ሕጋቸውን በተመለከተ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ።
30
አይሁድ ግን በዚህ ሰው ላይ ማሤራቸውን በተረዳሁ ጊዜ፣ ወዲያው ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም ከእርሱ ጋር ያላቸውን ክርክር ለአንተ እንዲያቀርቡ አዘዝኋቸው።
31
ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት፣ ጳውሎስን ይዘው በሌሊት እስከ አንቲጳጥሪስ ድረስ ወሰዱት።
32
በማግስቱም፣ ፈረሰኞቹ ብቻ እንዲያደርሱት አድርገው፣ ሌሎቹ ወደ ጦር ሰፈር ተመለሱ።
33
ፈረሰኞቹም ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ፣ ደብዳቤውን ለአገረ ገዡው ሰጡት፤ ጳውሎስንም አስረከቡት።
34
አገረ ገዥውም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ፣ ጳውሎስን ከየትኛው አውራጃ እንደ መጣ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣
35
“የአንተን ጕዳይ ከሳሾችህ ሲቀርቡ አያለሁ” አለው። ከዚያም ጳውሎስ በሄሮድስ ግቢ ውስጥ እንዲጠበቅ አዘዘ።
← Chapter 22
Chapter 24 →