bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Samuel 7
2 Samuel 7
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣
2
ነቢዩን ናታንን፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው።
3
ናታንም፣ “ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው።
4
በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤
5
“ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን፣ ‘ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤
6
እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም።
7
ከእስራኤላውያን ሁሉ ጋር በተጓዝሁበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው አንዱን፣ “ከዝግባ ዕንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?” ያልሁት አለን?’
8
“አሁንም ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤
9
በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤
10
የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፣ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከዚህ በፊት እንደ ሆነውም ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቍነውም፤
11
ለሕዝቤ ለእስራኤልም መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ሁሉ ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ እንዲሁም ከጠላቶችህ ሁሉ እጠብቅሃለሁ። “ ‘ እግዚአብሔር ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤
12
ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ፣ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።
13
ለስሜ ቤት የሚሠራ እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።
14
አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል ቢፈጽም ግን ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ።
15
ምሕረቴን ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ሁሉ ከእርሱ አላርቅም።
16
ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።’ ”
17
ናታንም የዚህን የጠቅላላውን ራእይ ቃል በሙሉ፣ ለዳዊት ነገረው።
18
ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው?
19
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው?
20
“ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህና!
21
ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል።
22
“ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! ከቶ የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።
23
“ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፣ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፣ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክታቸውን ከፊቱ አሳድዶ ታላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብፅም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ?
24
ሕዝብህን እስራኤልን ለዘላለሙ ያንተው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል።
25
“አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም ጠብቅለት፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤
26
ስለዚህ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሆናል፤ ሰዎችም፣ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ። የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።
27
“አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለባሪያህ ገልጸህለታል። ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ በልቡ ደፈረ።
28
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል፤
29
በፊትህ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር፣ አሁንም የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ። ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረካል።”
← Chapter 6
Chapter 8 →