bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Kings 16
2 Kings 16
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ።
2
አካዝ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት ያደረገውን መልካም ነገር በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት አላደረገም።
3
እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኩሰት ተከትሎ፣ ልጁን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
4
እንዲሁም ኰረብታ ላይ ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች፣ በኰረብታ ዐናቶችና ቅጠሉ በተንሰራፋው ዛፍ ሥር ሁሉ ሠዋ፤ ዕጣንም አጤሰ።
5
የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና አካዝን ለመክበብ ወጡ፤ ይሁን እንጂ ሊያሸንፉት አልቻሉም።
6
በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የይሁዳን ሰዎች አሳድዶ፣ ኤላትን ወደ ሶርያ ግዛት መለሰ፤ ከዚያም ኤዶማውያን ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ።
7
ከዚህ የተነሣም አካዝ፣ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር፣ “እኔ አገልጋይህም ልጅህም ነኝ፤ ስለዚህ መጥተህ ከሚወጉኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ሲል መልእክተኞች ላከበት።
8
አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብርና ወርቅ አውጥቶ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት ላከለት።
9
የአሦር ንጉሥም፣ የአካዝን ልመና በመቀበል፤ ደማስቆን አጥቅቶ ያዛት፤ ሕዝቧን ማርኮ ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው።
10
ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆም ያለውን መሠዊያ አይቶ፣ ንድፉን ከዝርዝር ጥናቱ ጋር ለካህኑ ለኦርያ ላከለት።
11
ካህኑ ኦርያም ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ዝርዝር ጥናት መሠረት መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከመመለሱም በፊት አጠናቀቀው።
12
ንጉሡ ከደማስቆ ተመልሶ በመጣ ጊዜ፣ መሠዊያውን አየ፤ ቀርቦም በመሠዊያው ላይ ወጣ፤
13
ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕቱንና የእህል ቍርባኑን በመሠዊያው ላይ አቀረበ፤ የመጠጥ ቍርባኑን አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቱንም ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ።
14
በአዲሱ መሠዊያና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መካከል፣ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የነበረውን የናስ መሠዊያ፣ ከቦታው አስነሥቶ ከአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው።
15
ከዚያም ንጉሥ አካዝ፣ ካህኑን ኦርያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በትልቁ አዲስ መሠዊያ ላይ የጧቱን የሚቃጠል መሥዋዕትና የማታውን የእህል ቍርባን፣ የንጉሡን የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን እንዲሁም የመላውን የአገሪቱን ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርብ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ደምና የሌላውን መሥዋዕት ደም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እርጨው፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ መመሪያ ለመጠየቅ የምጠቀምበት ይሆናል።”
16
ካህኑ ኦርያም ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
17
ንጉሡ አካዝም የጐንና የጐን ሳንቃዎቹን ነቅሎ ወሰደ፤ በተንቀሳቃሹ መቆሚያ ላይ ያሉትን የመታጠቢያ ሳሕኖች አስወገደ። የውሃ ማጠራቀሚያውን ክብ ገንዳ ከታች ተሸክመው ከያዙት ከዐሥራ ሁለቱ የናስ ቅርጽ ኮርማዎች ላይ አውርዶ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አስቀመጠው።
18
የአሦርንም ንጉሥ ለማስደሰት ሲል፣ በዕለተ ሰንበት ንጉሣዊ ዙፋን እንዲዘረጋበት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተሠራውን ከፍ ያለ ስፍራና ነገሥታቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚገቡበትን በውጭ ያለውን መግቢያ አነሣ።
19
በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
20
አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከእነርሱ ጋር በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ሕዝቅያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
← Chapter 15
Chapter 17 →