bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Kings 14
2 Kings 14
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ።
2
በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3
እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ዳዊት እንደ አደረገው ዐይነት አልነበረም፤ በማናቸውም ረገድ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ።
4
በየኰረብታው ላይ ያሉት ማምለኪያዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በየኰረብታው ላይ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
5
አሜስያስ መንግሥቱን አጽንቶ ከያዘ በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው፤
6
ይሁን እንጂ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እግዚአብሔር ፣ “እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል እንጂ አባቶች በልጆቻቸው፣ ልጆችም በአባቶቻቸው ኀጢአት አይገደሉ” ሲል ያዘዘ በመሆኑ፣ የነፍሰ ገዳዩን ልጆች አልገደላቸውም።
7
የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺሕ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው።
8
ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት ይዋጣልን” ሲል መልእክተኞች ላከበት።
9
የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ በሚስትነት ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው።
10
በርግጥ ኤዶምን ድል አድርገሃል፤ ልብህ አለመጠን አይኵራራ። ድል በማድረግህ አትንጠራራ፤ ዐርፈህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር የራስህን፣ የይሁዳንስ ውድቀት ለምን ትሻለህ?”
11
አሜስያስ ግን አልሰማም፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ጦርነት ገጠሙ።
12
ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
13
የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከ ተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ የሆነውን ቅጥር አፈረሰ።
14
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች ያለውን ወርቅና ብር በሙሉ፣ በዚያም የተገኘውን ዕቃ ሁሉ በመውሰድ ምርኮኞችንም ይዞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15
በዮአስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያደረገው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
16
ዮአስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
17
የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
18
በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
19
አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሤራ ስለ ጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ላኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉት ሰዎች ወደዚያው ልከው አስገደሉት፤
20
ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ መጥቶ በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።
21
ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት።
22
አሜስያስ ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ ነበር።
23
የኢዮስያስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ ነገሠ፤ አርባ አንድ ዓመትም ገዛ።
24
በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።
25
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በጋትሔፌር ነቢይ፣ በአማቴ ልጅ በባሪያው በዮናስ አማካይነት እንደ ተናገረው፣ ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ እስከ ሙት ባሕር ድረስ የነበረውን የእስራኤልን ድንበር ያስመለሰ ኢዮርብዓም ነው።
26
ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ፣ በእስራኤል የሚኖር ሁሉ እንዴት እጅግ ይሠቃይ እንደ ነበር እግዚአብሔር አየ፤ የሚረዳቸውም አልነበረም።
27
ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የእስራኤልን ስም ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋ ስላልተናገረ፣ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም አማካይነት ታደጋቸው።
28
በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ የፈጸመው ሁሉና ያደረጋቸው ጦርነቶች እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩትን ደማስቆንና ሐማትን እንዴት ለእስራኤል እንዳስመለሰ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
29
ኢዮርብዓም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ዘካርያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
← Chapter 13
Chapter 15 →