bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 34
2 Chronicles 34
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ።
2
እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳይል፣ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄደ።
3
በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ፣ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ።
4
በእርሱም ትእዛዝ የበኣሊም መሠዊያዎችን አፈራረሱ፤ እርሱም ከበላያቸው የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎችን አደቀቀ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶችን፣ ጣዖታቱንና ምስሎቹን ሰባብሮ ከፈጫቸው በኋላ፣ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነ።
5
የካህናቱን ዐጥንት በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ፤ በዚህ ዐይነትም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ።
6
እስከ ንፍታሌም ባሉ በምናሴ፣ በኤፍሬምና በስምዖን ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ የፈራረሱ አካባቢዎች፣
7
መሠዊያዎችንና የአሼራ ምስል ዐምዶችን አፈራረሰ፤ ጣዖታቱን እንደ ዱቄት አደቀቀ፤ በመላው እስራኤል የሚገኙትንም የዕጣን መሠዊያዎች አነካከተ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
8
ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፣ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዪቱን ገዥ መዕሤያንና የጸሓፊውን የኢዮአካዝን ልጅ ኢዮአክን የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይጠግኑ ዘንድ ላካቸው።
9
እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር።
10
እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እየተቈጣጠሩ እንዲያሠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ።
11
እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለዐናጢዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ።
12
ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣
13
የጕልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ።
14
ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።
15
ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።
16
ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤
17
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበረውንም ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።”
18
ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።
19
ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።
20
እርሱም ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም፣ ለሚክያስ ልጅ ለዓብዶን፣ ለጸሓፊው ለሳፋንና ለንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለዓሳያ ይህን ትእዛዝ ሰጠ፤
21
“ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ቅሬታዎች በተገኘው መጽሐፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቍጣ ፈስሷል፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።”
22
ኬልቅያስና ንጉሡ ከእርሱ ጋር የላካቸው ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደ ሆነችው ወደ ነቢዪቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍለ ከተማ ትኖር ነበር።
23
ነቢዪቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤
24
‘ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ።
25
እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና እጃቸው በሠራው ነገር ሁሉ ለቍጣ ስላነሣሡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’
26
እግዚአብሔርን ለመጠየቅ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ስለ ሰማኸው ቃል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
27
በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ስለ አዋረድህ፣ እንዲሁም በእኔ ፊት ራስህን ዝቅ ስላደረግህ፣ ልብስህንም በመቅደድ በፊቴ ስለ አለቀስህ፣ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር ።
28
እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ በዐይንህ አታይም።’ ” መልሷንም ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።
29
ከዚያም ንጉሡ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሰበሰበ።
30
እርሱም ከትንሽ እስከ ትልቅ ካሉት ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ሕዝብ፣ ከካህናትና ከሌዋውያን ጋር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ ለሕዝቡ አነበበላቸው
31
ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ እግዚአብሔርን ይከተል ዘንድ በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ትእዛዞቹን፣ ሕግጋቱንና ሥርዐቱን ለመጠበቅ፣ በዚህ መጽሐፍ ለተጻፈውም የኪዳን ቃል ለመታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን ዐደሰ።
32
ከዚህ በኋላ በኢየሩሳሌምና በብንያም የሚኖረው ሁሉ በዚህ ነገር ቃል እንዲገባ አደረገ፤ የኢየሩሳሌምም ሕዝብ የአባቶቹ አምላክ ባዘዘው የአምላክ ቃል ኪዳን መሠረት ፈጸሙ።
33
ኢዮስያስም አስጸያፊ ጣዖታትን ሁሉ ከመላው የእስራኤል ግዛት አስወገደ፤ በእስራኤል የነበሩትም ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ፤ እርሱ በሕይወት እያለም የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም።
← Chapter 33
Chapter 35 →