bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 31
2 Chronicles 31
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ፣ በዚያ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው፣ የማምለኪያ ድንጋዮችን ሰባበሩ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈረጡ፤ እንዲሁም በመላው ይሁዳና በብንያም፣ በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኰረብታ መስገጃዎችና መሠዊያዎች አጠፉ፤ እስራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ካጠፉ በኋላ ወደየከተሞቻቸውና ወደየርስታቸው ተመለሱ።
2
ሕዝቅያስ ካህናቱና ሌዋውያኑ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ እንዲያገለግሉና እንዲያመሰግኑ እንዲሁም በእግዚአብሔር ማደሪያ ደጆች ውዳሴውን እንዲዘምሩ፣ ካህናትንም ሆኑ ሌዋውያንን እያንዳንዳቸውን እንደየተግባራቸው በየክፍሉ መደባቸው።
3
በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ንጉሡ ጧትና ማታ እንደዚሁም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻውና በተወሰኑ በዓላት፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከራሱ ንብረት ሰጠ።
4
ካህናቱና ሌዋውያኑም ሙሉ ጊዜያቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጣቸው አዘዘ።
5
ትእዛዙ እንደ ወጣ እስራኤላውያን ወዲያውኑ የእህሉንና የአዲሱን ወይን ጠጅ፣ የዘይቱንና የማሩን እንዲሁም የዕርሻውን ፍሬ ሁሉ በኵራት በልግስና ሰጡ፤ ካላቸው ከማንኛውም ነገር ሁሉ ላይ እጅግ ብዙ የሆነ ዐሥራት አውጥተው አመጡ።
6
በይሁዳ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ከከብቶቻቸው፣ ከበግና ከፍየል መንጎቻቸውና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ከለዩአቸው የተቀደሱ ነገሮች ዐሥራት አውጥተው አመጡ፤ ከመሩትም።
7
ይህንም በሦስተኛው ወር ጀምረው፣ በሰባተኛው ወር አጠናቀቁ።
8
ሕዝቅያስና ሹማምቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።
9
ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቃቸው፤
10
ከሳዶቅ ቤተ ሰብ የሆነው ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስም፣ “ሕዝቡ ስጦታውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማምጣት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ በቂ ምግብ አግኝተናል፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለባረከም ይህን ያህል ብዛት ያለው ሊተርፍ ችሏል” አለ።
11
ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ጎተራ እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው፤ እነርሱም አዘጋጁ።
12
ከዚያም ስጦታውን፣ ዐሥራቱንና የተቀደሱ ስጦታዎቹን በታማኝነት አምጥተው አስገቡ። ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚሁ ዕቃዎች ኀላፊ ሲሆን፣ ወንድሙ ስሜኢ ደግሞ በማዕረግ ሁለተኛ ነበር።
13
ይሒዒል፣ ዓዛዝያ፣ ናሖት፣ አሣሄል፣ ይሬሞት፣ ዮዛባት፣ ኤሊኤል፣ ሰማኪያ፣ መሐትና በናያስ በንጉሡ ሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ በዓዛርያስ ተሹመው በኮናንያና በወንድሙ በሰሜኢ ሥር ሆነው ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።
14
የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው የሌዋዊው የይምና ልጅ ቆሬ ደግሞ በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር በቀረበው ስጦታ ላይ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትንም ነገሮች ለማከፋፈል፣ ኀላፊ ነበረ።
15
ዔድን፣ ሚንያሚን፣ ኢያሱ፣ ሸማያ፣ አማርያና ሴኬንያ በካህናቱ ከተሞች ተገኝተው፣ ለካህናት ወገኖቻቸው ለታላላቆቹም ሆነ ለታናናሾቹ፣ እንደየምድባቸው፣ በማከፋፈሉ ረገድ በታማኝነት ረዱት።
16
በተጨማሪም፣ ስማቸው በትውልድ መዝገቡ ውስጥ የነበረና የየዕለት ልዩ ልዩ ተግባራቸውን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው ለማከናወን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት ለሚችሉት፣ ዕድሜያቸው ሦስት ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ወንዶች ልጆች እንደዚሁ አከፋፈሉ።
17
በትውልድ መዝገብ በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ለገቡት ካህናት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ሌዋውያን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው አካፈሏቸው።
18
በዚህ የትውልድ መዝገብ ላይ የተዘረዘሩትን መላውን የማኅበረ ሰቡን ሕፃናት፣ ሚስቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ጨመሯቸው፤ ራሳቸውን በመቀደስ ታማኞች ነበሩና።
19
በከተሞቻቸው ዙሪያ ባሉት የዕርሻ ቦታዎች፣ ወይም በሌሎች ከተሞች ሁሉ ለሚኖሩት ለካህናቱ ለአሮን ዘሮች፣ በመካከላቸው ላሉት ወንዶችና በሌዋውያን የትውልድ መዝገብ ለተመዘገቡት ሁሉ እንዲያከፋፍሉ በየስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።
20
ሕዝቅያስ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካም፣ ቅንና ታማኝ ሆኖ በመገኘት በመላው ይሁዳ የፈጸመው ተግባር ይህ ነው።
21
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማገልገልም ሆነ፣ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ በመገዛት አንጻር ያደረገውን ሁሉ በፍጹም ልቡ አምላኩን በመፈለግ አከናወነ፤ ተሳካለትም።
← Chapter 30
Chapter 32 →