bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 28
2 Chronicles 28
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር እንዳደረገው እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም።
2
በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በኣሊምን ለማምለክም የተቀረጹ ጣዖታትን ሠራ።
3
እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያስወገዳቸውን አሕዛብ ልማድ በመከተል፣ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ዐጠነ፤ ወንዶች ልጆቹንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
4
በኰረብታ መስገጃዎችና በተራሮች ዐናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ።
5
ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም ብዙዎቹን ምርኮኞች አድርገው ወደ ደማስቆ ወሰዷቸው። ደግሞም ለእስራኤል ንጉሥ ዐልፎ ተሰጠ፤ እርሱም ከባድ ጕዳት አደረሰበት።
6
ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺሕ ወታደሮች ገደለ።
7
ጦረኛው ኤፍሬማዊ ዝክሪም የንጉሡን ልጅ መዕሤያን፣ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን ዓዝሪቃምንና ለንጉሡ በማዕረግ ሁለተኛ ሰው የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።
8
እስራኤላውያንም ከገዛ ወገኖቻቸው ሁለት መቶ ሺሕ ባለ ትዳር ሴቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ማረኩ፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
9
ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚያ ስለ ነበር፣ ሰራዊቱ ወደ ሰማርያ በተመለሰ ጊዜ ለመቀበል ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ እናንተ ግን እስከ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ፈጃችኋቸው።
10
አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች፣ ባሪያዎቻችሁ ልታደርጓቸው ትፈልጋላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ ኀጢአት ሠርታችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አልበደላችሁምን?
11
እንግዲህ ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቍጣ በእናንተ ላይ ነድዷልና፣ በምርኮ ያመጣችኋቸውን ወገኖቻችሁን መልሷቸው።”
12
ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣
13
“እነዚህን ምርኮኞች እዚህ ማምጣት አልነበረባችሁም፤ አለዚያ እኛ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንሆናለን፤ በኀጢአታችንና በበደላችን ላይ ሌላ ልትጨምሩ ታስባላችሁን? በደላችንማ ቀድሞውኑ በዝቷል፤ ቍጣውም በእስራኤል ላይ ነውና” አሉ።
14
ስለዚህ ወታደሮቹ በሹማምቱና በጉባኤው ሁሉ ፊት ምርኮኞቹን ለቀቁ፤ የተማረከውንም ዕቃ መለሱ።
15
በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቍታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
16
በዚያን ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤
17
ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና።
18
ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በየኰረብታው ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ያሉትን ከተሞች በመውረር ቤትሳሚስን፣ ኤሎንን፣ ግዴሮትን፣ ሦኮን፣ ተምናን፣ ጊምዞንና በአካባቢአቸው የሚገኙትን መንደሮች ሁሉ ያዙ፤ ተቀመጡባቸውም።
19
የእስራኤል ንጉሥ አካዝ ክፋትን በይሁዳ ምድር ስላስፋፋና ለእግዚአብሔርም የነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ደረጃ ስላጓደለ፣ እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደ።
20
የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም።
21
አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ጥቂት ዕቃዎች ወስዶ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶ ነበር፤ ይህም አልረዳውም።
22
ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜም፣ ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነቱን ከምን ጊዜውም ይበልጥ አጓደለ፤
23
እርሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለ ረዷቸው፣ እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ሲል እርሱን ላሸነፉት የደማስቆ አማልክት መሥዋዕት አቀረበ።
24
አካዝ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ ወሰደ ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጎዳናው ማእዘን ላይ መሠዊያ አቆመ።
25
በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቃጥልባቸውን የኰረብታ መስገጃዎች ሠራ፤ በዚህም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ አነሣሣው።
26
በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባርና አካሄዱ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።
27
አካዝ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በኢየሩሳሌምም ከተማ ተቀበረ፤ የተቀበረው ግን በእስራኤል ነገሥታት መካነ መቃብር አልነበረም። ልጁ ሕዝቅያስም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
← Chapter 27
Chapter 29 →