bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 26
2 Chronicles 26
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት።
2
አሜስያስ እንደ አባቶቹ ሁሉ ካንቀላፋ በኋላ፣ ኤላትን እንደ ገና የሠራት፣ ወደ ይሁዳም የመለሳት ዖዝያን ነበር።
3
ዖዝያን በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
4
እርሱም አባቱ አሜስያስ እንደ አደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
5
እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።
6
በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጌትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ።
7
እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን፣ በጉርበኣል በሚኖሩ ዐረቦችና በምዑናውያን ላይ ድልን አቀዳጀው።
8
አሞናውያን ለዖዝያን ግብር ገበሩለት፤ ኀይሉ ስለ ገነነም ዝናው እስከ ግብፅ ዳርቻ ወጣ።
9
ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማእዘኑ በር፣ በሸለቆው በርና በቅጥሩ ማዕዘን ማማዎች ሠርቶ መሸጋቸው።
10
እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጕድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሠራተኞች ነበሩት።
11
ዖዝያን ከንጉሡ ሹማምት አንዱ በሆነው በሐናንያ መሪነት፣ በጸሓፊው በይዒኤልና በአለቃው በመዕሤያ አማካይነት ተሰብስቦ በተቈጠረው መሠረት በየምድቡ ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ የሚወጣ፣ በሚገባ የሠለጠነ ሰራዊት ነበረው።
12
በተዋጊዎቹ ላይ የተሾሙት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ጠቅላላ ቍጥር ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ነበር።
13
በእነዚህም የሚመራ ሦስት መቶ ሰባት ሺሕ አምስት መቶ ሰው ያለው ሰራዊት አለ፤ ይህም ንጉሡ በጠላቶቹ ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ለመሰለፍ የሚበቃ ጠንካራ ኀይል ነበር።
14
ዖዝያን ለሰራዊቱ ሁሉ ጋሻ፣ ጦር፣ የራስ ቍር፣ ጥሩር፣ የቀስት ማስፈንጠሪያ ደጋንና የሚወነጨፍ ድንጋይ አደለ።
15
በኢየሩሳሌምም፣ ንድፎቻቸው በባለሙያዎች የተዘጋጁ፣ በመጠበቂያ የግንብ ማማዎችና በየማእዘኑ መከላከያዎች ላይ ፍላጻ የሚስፈነጠርባቸውንና ትልልቅ ድንጋዮች የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አሠራ። እስኪበረታም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለ ታገዘ፣ ዝናው በርቀትና በስፋት ተሰማ።
16
ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ አምላኩን እግዚአብሔርን በደለ፤
17
ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋር ተከትሎት ገባ።
18
እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት።
19
ጥና በእጁ ይዞ ዕጣን ለማጠን ዝግጁ የነበረው ዖዝያን ተቈጣ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው ፊት ሆኖ ካህናቱ ላይ እየተቈጣ ሳለ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት።
20
ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስና ሌሎቹ ካህናት ሁሉ በተመለከቱት ጊዜ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ እንደ ወጣበት አዩ። ስለዚህ አጣድፈው አስወጡት፤ በርግጥ እርሱም ራሱ ለመውጣት ቸኵሎ ነበር፤ እግዚአብሔር አስጨንቆታልና።
21
ንጉሥ ዖዝያን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለምጻም ነበረ። ለምጻም በመሆኑም ከቤተ መቅደስ ተወግዶ ነበርና በተለየ ቤት ተቀመጠ ። ከዚያም ልጁ ኢዮአታም የቤተ መንግሥቱን አስተዳደር በኀላፊነት ተረክቦ የአገሩን ሕዝብ ይመራ ጀመር።
22
በዖዝያን ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነውን ሌላውን ተግባር ሁሉ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎታል።
23
ዖዝያንም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ። ሕዝቡም “ለምጽ አለበት” ብለው የነገሥታቱ በሆነው መቃብር አጠገብ ባለው ቦታ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
← Chapter 25
Chapter 27 →