bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 24
2 Chronicles 24
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አርባ ዓመት ገዛ። እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች።
2
ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ።
3
ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለደ።
4
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ወሰነ።
5
ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦም፣ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በየዓመቱ ለማደስ ገንዘብ ከእስራኤል ሁሉ ሰብስቡ፤ ይህንም አሁኑኑ አድርጉት” አላቸው። ሌዋውያኑ ግን ቸል አሉ።
6
ስለዚህ ንጉሡ ሊቀ ካህኑን ዮዳሄን ጠርቶ፣ “ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና የእስራኤል ጉባኤ ለምስክሩ ድንኳን እንዲወጣ የወሰኑትን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላተጋሃቸው ለምንድን ነው?” አለው።
7
በዚህ ጊዜ የዚያች ክፉ የጎቶልያ ልጆች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሰብረው በመግባት የተቀደሱ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ለበኣል ጣዖታት አገልግሎት እንዲውሉ አድርገው ነበር።
8
በንጉሡም ትእዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በር አጠገብ በውጭ በኩል አኖሩት።
9
ከዚህ በኋላ እስራኤል በምድረ በዳ ሳሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ።
10
ሹማምቱ ሁሉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ግብሩን በደስታ አመጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጨመሩ።
11
ሣጥኑ በሌዋውያኑ እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በሚደርስበት ጊዜ፣ እነርሱም በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም ይመጡና ሣጥኑን አጋብተው ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። ይህን በየቀኑ በማድረግ እጅግ ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ።
12
ንጉሡና ዮዳሄም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን አስረከቧቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ድንጋይ ጠራቢዎችንና ዐናጢዎችን እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመጠገን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ቀጠሩ።
13
በሥራው ላይ የተሰማሩት ሰዎች ትጉሃን ስለ ነበሩ፣ ሥራው በእጃቸው ተከናወነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀደም ሲል በነበረው ዐይነት ዐደሱት፤ አጠናከሩትም።
14
ከጨረሱም በኋላ ቀሪውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ በገንዘቡም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ማለትም ለአገልግሎትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚውሉ ዕቃዎች እንደዚሁም ጭልፋዎችና ሌሎች የወርቅና የብር ዕቃዎችም ተሠሩ። ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ይቀርብ ነበር።
15
ዮዳሄ ሸምግሎ ዕድሜ ከጠገበ በኋላ፣ በመቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ።
16
እርሱም በእስራኤል ውስጥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ መልካም ሠርቷልና በዳዊት ከተማ በነገሥታቱ መቃብር ተቀበረ።
17
ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ ሹማምት መጥተው ለንጉሡ ታማኝነታቸውን ገለጡ፤ ንጉሡም አደመጣቸው።
18
እነርሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ትተው፣ የአሼራን ዐምዶችና ጣዖታትን አመለኩ፤ በበደላቸውም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።
19
ወደ እግዚአብሔር ይመልሷቸው ዘንድ እርሱ ነቢያቱን ወደ ሕዝቡ ሰደደ፤ ነቢያቱም መሰከሩባቸው፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም።
20
የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቷችኋል” አላቸው።
21
እነርሱ ግን አሤሩበት፤ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።
22
ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ በዚህ ፈንታ ልጁን ገደለው፤ በሚሞትበትም ጊዜ፣ “ እግዚአብሔር ይየው፤ እርሱው ይበቀልህ” አለ።
23
በዓመቱም መጨረሻ ፣ የሶርያ ሰራዊት በኢዮአስ ላይ ዘመተ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም ወርሮ የሕዝቡን መሪዎች ሁሉ ደመሰሰ፤ ምርኮውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላከ።
24
የሶርያ ሰራዊት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር በጣም የሚበልጠውን ሰራዊት በእጃቸው አሳልፎ ሰጠ፤ ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ በኢዮአስ ላይ ተፈረደበት።
25
ሶርያውያንም በወጡ ጊዜ ኢዮአስን ክፉኛ አቍስለው፣ ጥለውት ሄዱ፤ የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ስለ ገደለም፣ ሹማምቱ አሢረውበት በዐልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በዳዊት ከተማ ተቀበረ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልተቀበረም።
26
በእርሱ ላይ ያሤሩትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቱ የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ።
27
የወንዶች ልጆቹ ታሪክ፣ ስለ እርሱ የተነገሩት ብዙ ትንቢቶችና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መታደስ በነገሥታቱ የታሪክ መዛግብት ተጽፈዋል። ልጁ አሜስያስም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
← Chapter 23
Chapter 25 →